የኢትዮጵያና ሶማሊያ መሪዎች ከሞቃዲሾ ውይይታቸው በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ ምን አሉ?
መሪዎቹ የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል በአንካራ የተጀመረውን የቴክኒክ ቡድን ንግግር አድንቀዋል

የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አዛዦች የደረሱት ስምምነትም በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ዛሬ በሞቃዲሾ ተገናኝተው መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከአንድ አመት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረታቸውን ለማርገብ በቱርክ አደራዳሪነት ከተስማሙ በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በሞቃዲሾ ጉብኝት ያደረጉት።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ከውይይቱ በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ የዛሬው ምክክር ባለፉት ወራት ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለማደስ ያካሄዷቸውን ተከታታይ ውይይቶች ያጸና መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው የጠቆመው መግለጫው፥ ሀገራቱ በዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትብብራቸውን በማስፋት የርስ በርስ መተማመን መገንባት እንዳለባቸው አጽንቆት ሰጥቶታል።
ሀገራቱ የጋራ እጣ ፈንታ ያላቸው ሉአላዊ ሀገራት መሆናቸውን በመጥቀስም ለቀጠናው መረጋጋትና እድገት በጋራ ለመስራት መሪዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው የጠቀሰው።
የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክሩና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጎለብቱ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት መስማማታቸውንም አብራርቷል።
መሪዎቹ የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል በቱርክ በተደረሰው ስምምነት መሰረት (አንካራ ዲክላሬሽን) የቴክኒክ ቡድን ንግግር መጀመሩንም ያደነቁ ሲሆን፥ ለገንቢ ንግግርና ትብብር ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አዛዦች የደረሱት ስምምነትም በቀጠናው መረጋጋት ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
የሀገራቱ የጦር መሪዎች በቅርቡ ባደረጉት ምክክር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ እንዲሰማራ መስማማታቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች ለሀገራቱ የጋራ ፍላጎት፣ ሰላምና መረጋጋት በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ባወጡት የጋራ መግለጫ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሻከሩ ይታወሳል።
ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው ውጥረት በቱርክ አደራዳሪነት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአንካራ ፊትለፊት ከተገናኙ በኋላ መርገቡም አይዘነጋም።
በአንካራው ስምምነት መሰረትም የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ባለፉት ወራት በሞቃዲሾ እና በአዲስ አበባ በመገናኘት ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በጥር ወር መጀመሪያ በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።