ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር ለምን በሶማሊያ ላይ ልዩ ትኩረት እንዲያደርግ አዘዙ?
የአሜሪካ ጦር ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያውን ጥቃት በሶማሊያዋ ፑንትላድ ፈጽሟል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/08/258-164137-whatsapp-image-2025-02-08-at-3.40.43-pm_700x400.jpeg)
አብዛኞቹ የአይኤስ- ሶማሊያ ተዋጊዎች ኢትዮጵያዊን ናቸው ተብሏል
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር ለምን በሶማሊያ ላይ ልዩ ትኩረት እንዲያደርግ አዘዙ?
ከሰሞኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸው አየር ሀይል በፑንትላድ መሰረቱን አድርጓል በተባለው የአይኤስ-ሶማሊያ ቡድን ይዞታዎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት አወድሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ዳግም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያ የውጭ ሀገራ ወታደራዊ ጥቃታቸውን በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡
በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ የሚባሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራስ ገዝ ነኝ በምትለው ፑንትላንድ ተራራማ ቦታዎች ላይ መሽገዋል በተባሉት የአይኤስ አመራሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ይህን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለምን ሶማሊያ ላይ ትኩረት አደረጉ? የሚለው ሀሳብ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡
ማት ብሪያን መሰረቱን ኬንያ ባደረገ አንድ የአፍሪካ ጸጽታ እና ደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ ሲሆን ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ አይኤስ-ሶማሊያ በአፍሪካ ትልቁ የአይኤስ መሰረት መሆኑን ተናግሯል፡፡
እንደ ተንታኙ ከሆነ ምስራቃዊ የሶማሊያ ተራሮች ስር የመሸገው የአይ ኤስ ሶማሊያ ቡድን ሰንሰለቱ እስከ ሞዛምቢክ እና ማሊ ድረስ የተዘረጋ መሆኑ፣ አይኤስ በአፍሪካ ለሚፈጽማቸው ተልዕኮዎች የገንዘብ እና ስምሪት ማዕከል እንደሆነም ተናግሯል፡፡
አይኤስ-ሶማሊያ በተለይም ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ አረብ ሀገራት የሚጓዙ ወጣት ኢትዮጵያዊያንን በአማላይ ገንዘብ እየመለመለ መሆኑን፣ በሰው ሀይል እና በቴክኖሎጂም የበለጠ እየተደራጀ መጥቷል ተብሏል፡፡
በዋሸንግተን በሚገኘው የአሜሪካ ዩንቨርሲቲ ማዕከል ውስጥ የጸረ ሽብር ፖሊሲ ዳይሬክተር የሖኑት ትሪሲያ ባኮን በበኩላቸው አይኤስ ሶማሊያ በርካታ ተዋጊዎች ከሰሜን አፍሪካ ሀገራት እየተቀላቀሉ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት አሜሪካ በአየር ጥቃት ገድየዋለሁ ያለችው አብዱል ቃዲር ሙሚን የአይኤስ ዋና አዛዥ ስለመሆኑም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም በኢራን ይደገፋል የሚባለው የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን ከአይኤስ ሶማሊያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠሩን እና የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ እያገኘ ነውም ተብሏል፡፡
ይህ መሆኑ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ እና አካባቢው የአሜሪካ አጋር የሖኑ ሀገራትን ደህንነት የሚያሰጋ ነው መባሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦራቸው በዚህ ቡድን ላይ እርምጃ እንዲወስድ ለማዘዛቸው ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ከወራት በፊት ከሶማሊያ ፌደራል መንግስት ራሷን እንዳገለለች የምትናገረው ፑንትላንድ በአይኤስ ቡድን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረች ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት የአካባቢውን ወታደራዊ መሪ መማረኳን አስታውቃለች፡፡
የራስ ገዟ ፑንትላንድ የጸጥታ ሃላፊ መሀመድ ሙባረክ በበኩላቸው ፑንትላንድ በራሷ አቅም አይኤስን ስትዋጋ መቆየቷን ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቡድኑ አቅም እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ከኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና የተወሰኑ ሌሎች ሀገራት በስተቀር ድጋፍ ያደረገላቸው አካል እንደሌለ የሚናገሩት ሀላፊው አሜሪካ የጀመረችውን ድጋፍ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ቡድኑ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበርካታ ሀገራት የመጡ ታጣቂዎች እየተቀላቀሉት ነው የተባለ ሲሆን ቀላል የማይባሉ ወታደራዊ አመራሮች ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
80 በመቶ የአይኤስ ተዋጊዎች ሶማሊያዊያን አይደሉም የተባለ ሲሆን በተለይም ከታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ ሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዝያ እና የመን ዜግነት ያላቸው ናቸውም ተብሏል፡፡