ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን የወደብ ስምምነት በመግለጫ ጋጋታ እንደማታቆም ገለጸች
ሚንስቴሩ ግብጽ ለኢትዮጵያ አለመረጋጋት በቀጥታም በተዘዋዋሪም እየሰራች መሆኗን አስታውቋል
ከካይሮ የሚደመጡ ተደጋጋሚ እና ተመሳሳይ መግለጫዎች ለውጥ እንደማያመጡም ተገልጻል
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን የወደብ ስምምነት በመግለጫ ጋጋታ የሚቆም እንዳልሆነ ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም በመግለጫቸው ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊያ የመግባቢያ ስምምነት ዋነኛው ነው።
አረብ ሊግን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት በመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ መግለጫ ማውጣታቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱት ጫና ምንድን ነው? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ "ኢትዮጵያ በመግለጫ ጋጋታ የምትረበሽ ሀገር አይደለችም" ሲሉ አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "ከካይሮ ለዓመታት ተመሳሳይ መግለጫዎች ሲወጡ ነበር፣ የጦርነት ነጋሪት ሳይቀር በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሲተላለፍም ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን አላቆመችም፣ አሁንም በመግለጫ የሚቆም እና የሚሸበር የለም" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች፣ በመግለጫ እምሸበር ሀገር እና ህዝቦች አይደለንም" ያሉት አምባሳደር መለስ የኢትዮጵያ ጥያቄ የፍትህ ነው ጉዳዩን የማስረዳት የዲፕሎማሲ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም በምላሻቸው ላይ ጠቅሰዋል።
"ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየሰራች ነው" ያሉት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ለብቻዬ ልጠቀም በሚል ያቀረበችው ጥያቄ እንደሌለም አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ኳታርን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት" ኢትዮጵያ ወደብ ብታገኝ እንደማይቃወሙ ነገር ግን የሌላ ሀገር ሉዓላዊነትን ባልጣሰ መንገድ መሆን አለበት" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት እንዳትተገብሪው ያለችው ሶማሊያ ጉዳዩን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
አምባሳደር መለስ በመግለቻቸው ላይ ያነሱት ጉዳይ 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲሆን ጉባኤው ከየካቲት 9 እስከ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ብለዋል።
ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።