ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በወደብ ጉዳይ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች
ሶማሊያ የግብፅ ወታደሮች ወደ ግዛቷ እንዲመጡ ፈቅዳለች?
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትላት ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ከሰሞኑ ግብጽን የጎበኙት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በኳታርም ተመሳሳይ ጉብኝት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት "እንዳትተገብሪው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ወደ ካይሮ ተጉዘው ከግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸውን ገልጸው "ወታደራዊ ስምምነትን በሚመለከት አልተወያየንም፣ የግብጽ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እየገቡ ነው መባሉ ስህተት ነው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያን ስምምነቱን እንዳትተገብሪው እያልን ያለነው ግን ወደ ወታደራዊ ስምምነት እንዳንሄድ ነው" ሲሉም ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን ከመፈራረማቸው ጥቂት ቀናት በፊት በጅቡቲ በአካል ተገናኝተው እንደነበር እና እንደከዷቸውም በቃለ መጠይቁ ላይ ገልጸዋል።
አሁን ጉዳዩ በኢትዮጵያ እጅ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ጉዳዩን ሁላችንንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መፍታት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ ወደብ ቢኖራት ተቃውሞ የለንም፣ ለድርድርም ዝግጁ ነን ነገር ግን የሌላ ሀገር ግዛትን በመውሰድ ግን ሊሆን አይገባም" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚንስትር የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሰሞኑ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መረጋጋት ልጆቿን እንደገበረች፣ የሰሞንኛው የአለንልሽ ድጋፍም ሶማሊያን ከመጥቀም አንጻር ሳይሆን ኢትዮጵያን ከመጥላት የመነጨ እንደሆነ በኤክስ አካውንታቸው ላይ አጋርተዋል።