ባለ ሁለት ሞተር የሆነው “su-30” በአንድ ተልእኮ እስክ 3 ሺህ ኪ.ሜ ማካለል ይችላል
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ባሳለፍነው ሳምንት ዘመናዊ የሆነውን የsu-30 ተዋጊ ጀቶች ን እንደታጠቀ ማስታወቁ ይታወሳል።
በርክክቡ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ “ተቋሙ የተረከባቸው ዘመናዊ “su-30” የጦር ጀቶች በተመሳሳይ ጊዜ በአየርና በምድር ላይ ያለ የጠላት ኢላማንን ማውደም የሚችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ባለ ሁለት ሞተር የሆነው “ሱኩሆይ ኤስዩ-30” የጦር ጄት ምርት የተጀመረው በፈረንጆቹ 1996 ሲሆን፤ “su-30” የሚል መጠሪያውን ያገኘው በፈረንጆቹ 1996 እንደሆነ ይነገራል። የsu-30 ተዋጊ ጀቶች በምእራባውያን ዘንድ “Flanker-C” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
ሩሲያ እስካሁን 200 የsu-30 ተዋጊ ጀቶችን ያመረተች ሲሆን፤ ህንድም በሩሲያ ፈቃድ “ኤስዩ- 30” የጦር ጄቶች ማምረት እንደመጀመረች የሚሊተሪ ቱዴይ መረጃ ያመለክታል።
የሩሲያ የአየር ኃይል አሁን ላይ የጦር ጄቱን እየተጠቀመበት ይገኛል። ቻይና፣ ህንድኢንዶኔዢያ፣ ማዢያም የጦር ጄቱን የታጠቁ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በቅርቡ እንዚህን ሀገራት ተቀላቅላለች።
“ሱኩሆይ ኤስዩ- 30” ምን የተለየ ነገር ይዟል?
ሩሲያ ሰራሹ “ሱኩሆይ ኤስዩ-30” የጦር ጄት በአየር ላይ ውጊያ እንዲሁም ከአየር ወደ ምድር ለሚደረግ ዉጊያም ጥቅም ለይ የሚውል የጦር አውሮፕላን ነው።
ከችሎታ አንፃር su-30 ከአሜሪካው F-15E ስትራይክ ኤግል ከሚባለው የጦር ጄት ጋር በስፋት ይመሳሰላል።
ኤስዩ- 30 የጦር ጄት አብሮት የተሰራ ባለ 30 ሚሜ “GSh-301” መድፍ ከ150 ጥይቶች ጋር የታጠቀ ነው።
ከአየር ወደ አየር፤ ከአየር ወደ ምድር የሚተኩ ሚሳኤሎች፣ ክላስተር እና በሌዘር የሚመሩ ቦምቦች እንዲሁም ሮኬቶችን ጨምሮ እስከ 8 ሺህ ኪሎ ግም የሚደርስ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቅ የሚችል ነው።
ሁለት ቱርቦፋን ሞተር የተገጠመለት የጦር ጄቱ፤ በአንድ ተልእኮ ሰፊ አካባቢን ማካለል እንደሚችልም ይነገራል።
የጦር አውሮፕላኑ መያዝ በሚችለው መደበኛ ነዳጅ በአንድ ተልእኮ እስክ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ማካለል የሚችል ሲሆን፤ በዚህም ከ4 እስከ 5 ሰዓት የውጊያ ተልእኮ ማከናወን ይችላል።
በአየር ላይ ነዳጅ ከተሞላት ደግሞ በአንድ ተልእኮ እስክ 5 ሺህ 200 ኪ.ሜ ማካለል የሚችል ሲሆን፤ እስከ 10 ሰዓት የውጊያ ተልእኮ ማከናወን ይችላል።
በአንድ ጊዜ 2 ሰዎችን የሚያሳፍረው ጦር ጄቱ በሰዓት እስከ 2 ሺህ 120 ኪሎ ሜትር ድረስ መብረር እንደሚችልም ነው የተነገረው።