ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር አሳን ልማልማት የሚያስችሉ ሁለት ፕሮጄክቶችን ጀመረች
ፕሮጄክቶቹ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚተገበሩ ናቸው
ኢትዮጵያ በዓመት 95 ሺህ ቶን አሳ የማምረት አቅም አላት
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሳን በዘላቂነት ልማልማት የሚያስችሉ ሁለት አዳዲስ ፕሮጄክቶችን ጀመረች።
ፕሮጄክቶቹ ለቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የሚዘልቁ ሲሆን ከጎረቤት ሐገራት ጋር በመተባበር የሚተገበሩ ናቸው ተብሏል።
የመጀመሪያው የባሮ-አኮቦ-ሶባት የአሣ ልማት ፕሮጄክት ሲሆን ከደቡብ ሱዳን ጋር በመተባበር የሚተገበር ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በኦሞ-ቱርካና ተፋሰስ ከኬንያ ጋር በመተባበር የሚተገበር ነው።
ሁለቱም ፕሮጄክቶች በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ድጋፍ የሚተገበሩ ናቸው።
በኢጋድ አባል ሃገራት በዓመት እስከ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን አሳ ለማምረት የሚያስችል እምቅ ተፈጥሯዊ አቅም አለ።
ሃገራቱ የሚገኙበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከታላላቅ ውቅያኖሶች ጋር የሚዋሰን ብቻም ሳይሆን በርካታ ውሃማ አካላትን የያዘ ነው።
ከ8ቱ የኢጋድ አባል ሃገራት 5ቱ ብቻ በድምሩ 7 ሺ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚጠጋ የባህር ዳርቻ አላቸው። ይህ የአሳ ሃብት ልማትን በስፋት ለማከናወን የሚያስችል ነው። ይህንኑ የተመለከተ ወርክሾፕም በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
በወርክሾፑ የተገኙት የኢጋድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ መሪ ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ዓመታዊ ምርቱን እስከ 2 ነጥብ ሚሊዮን ቶን ለማድረስ የሚያስችል ዐቅም አለ ብለዋል፤ በሃገራቱ ከፍተኛ የምርቱ ፍላጎት ቢኖርም ህገ ወጥ ማስገር ችግር መሆኑን በመጠቆም።
በወርክሾፑ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለአሳ ሃብት ልማት የሚሆን ሰፊ አቅም ካላቸው የኢጋድ አባል ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን በመጥቀስ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ያለውን ሃብት አልምቶ ለመጠቀም ከኢጋድ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በባሮ-አኮቦ-ሶባት እና በኦሞ-ቱርካና ተፋሰስ ከጎረቤት ሃገራት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለፁት።
በሚኒስቴሩ የአሳ ሐብት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሁሴን አበጋዝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዓመት 95 ሺ ቶን የማምረት አቅም እንዳላት ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አቶ ሁሴን ከዚህ ውስጥ አሁን በዓመት እየተመረተ ያለው እስከ 70 ሺ ቶን ድረስ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን ሃብቱ በተወሰኑ አስጋሪዎች ብቻ የሚመረት እና የማምረቻ መሳሪያዎች እጥረት መኖሩን ገልፀዋል።
ማስገርን የተመለከተ ራሱን የቻለ መመሪያ እና ህግ አለመኖሩ ለህገ ወጥ አስጋሪዎች መበራከት ምክንያት መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ሆኖም አሁን ሃብቱን ለንግድ ሊሆን በሚችል መልኩ በሰው ሰራሽ መንገዶች ጭምር በስፋት ለማምረት 5 ሺ ኩሬዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።