ኢጋድ “ብሉ ኢኮኖሚ” ቢተገበር ኖሮ የእምቦጭ አረም `አይከሰትም ነበር አለ
“ብሉ ኢኮኖሚ” ስትራቴጂ እምቦጭ አረምን ለመከላከል እንደሚሰራም ኢጋድ አስታውቋል
“ብሉ ኢኮኖሚ” የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ነው
በአፍሪካ ትልልቆቹ ኃይቆች የሚገኙበት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በቀጠናው ያለውን የውኃ ሃብት በአግባቡ እንደሚጠቀም አስታውቋል።
ከውኃ ጋር የተሳሰረ ኢኮኖሚ ወይም ውኃ ወለድ ኢኮኖሚን ተግባራዊ እንደሚያደርግ የገለጸው ድርጅቱ ለዚህ የሚሆነውን “ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ” ለመተግበር መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።
ለአምስት ዓመታት እንደሚተገበር የተገለጸው የኢጋድ ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በሁሉም ውኃማ አካላት ላይ እንደሚተገበር ተገልጿል።
የኢጋድ አባል ሀገራት ባለፈው አርብ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ላይ የብሉ ኢኮኖሚን ለመተግበር ቁርጠኞች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ እና የብሉ ኢኮኖሚ አስተባባሪ እሸቴ ደጀን (ዶ/ር) ከውኃ ጋር የተሳሰረ ኢኮኖሚ ወይም ውኃ ወለድ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ሲደረግ የአካባቢ ጥበቃም አብሮ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሁለቱንም የዓባይ መነሻ ትልልቅ ሃይቆች (ቪክቶሪያ እና ጣና ኃይቅን) ያቀፈ ሲሆን፤ ከነዚህ ውሃማ አካላት ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ፈተናዎች እንዳሉ ገልጿል።
መካከል አንዱ ውሃማ አካላትን በአግባቡ ጥቅም እንዲሰጡ አለማድረግ ከፈተናዎች መካከል ይጠቀሳልም ተብሏል።
እሸቴ ደጀን (ዶ/ር)፤ የውኃ አካላት የሚሰጡት አገልግሎት ብዙ በመሆኑ ለትራንስፖርት አገልግሎት በሚውሉበት ጊዜ ጥቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። ከውሃማ አካላት አሸዋ ሲወጣና ኤሌክትሪክ ሲመነጭ የአካባቢ ጥበቃ መርህ ሊጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለአብነት ውሃን ከጣና ሃይቅ በመውሰድ በበለስ ኤሌክትሪክ ሲመነጭ የሃይቁ የውሃ መጠን ቀንሶ የሃይቁ ዳርቻ ለእምቦጭ አረም ሊወረር እንደሚችል ያነሳሉ። ይህንን ለማስቀረትም በውሃ ላይ የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እቅስቃሴዎች “ተናበው መከናወን አለባቸው” ብለዋል ዶ/ር እሸቴ።
በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን እምቦጭ በተመለከተ እርሳቸው ቀደም ብሎ ይሰሩበት በነበረው የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትት ውስጥ ሆነው ችግሩ ሊከሰት እንደሚችል መናገራቸውን ጠቅሰዋል።
በወቅቱ ችግሩን ለመፍታት ክልላዊ ቡድን ተቋቁሞ እንደነበር ያነሱት አስተባባሪው ``ጣና ታሟል`` የሚል ጹሁፍ አቅርበው እንደነበርም አንስተዋል።
ብሉ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል ኖሮ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በተለያዩ ሃይቆች ላይ የተከሰተውና እየተከሰተ ያለው የእምቦጭ አረም እንደማይከሰትም አስተባባሪው ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ብሉ ኢኮኖሚ ተፈጥሮ ሀብቱ እንዲጠበቅ ስለሚያደርግ እንደ እምቦጭ ያለ መጤ አረምን መቋቋ እንደሚቻልም ነው የተናገሩት። በጣና ኃይቅ ላይ ብዙ ያልተወራለት አዞላ የሚባል አረምም አሁን ላይ መኖሩን ዶ/ር እሸቴ ገልጸዋል።
በኢጋድ ብሉ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ተጠሪ እና በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የዓለም አቀፍ ማሪታይ ሕግ ባለሙያ አነኔ ቀጄላ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ``ብሉ ኢኮኖሚ``ን ተግባራዊ ለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን ያነሳሉ።
ግልጽ የሆነ ራዕይ ያለመኖር፤ የዕውቀትና የግንዛቤ ችግር መኖር፤ በመንግስት መዋቅር ላይ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸው ዕውቀት አናሳ መሆንና የገንዘብ ችግር ተጠቃሽ ችግሮች እንደሆኑ ነው ባለሙያዋ ለአል ዐይን አማርኛ የገለጹት።
በቀጣናው ብሉ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ለማድረግ አሁን ላይ በተለያዩ ሀይቆች እየተስፋፋ ያለው የእምቦጭ አረም እንቅፋት እንደሆነ ዶ/ር እሸቴ እንዳነሱት ሁኑ አነኔም ይገልጻሉ፡፡
“ብሉ ኢኮኖሚ” ስትራቴጂ የእምቦጭ አረምን መከላከል እንዲችል ትኩረት መደረጉንም አነኔ ቀጄላ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ባለሙያዋ፤ እምቦጭ አረም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ችግር በመሆኑ የውሃ መጠንን እንደሚቀንስ ያነሱ ሲሆን ይህም ውሃማ አካላት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጡ እና አካባቢ ለቱርዝም ምቹ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
አምቦጭ ለማስወገድ ከህንድ እና ሱዳን ልምድ መቅሰም ይገባል ያሉት አነኔ ቀጄላ ብሉ ኢኮኖሚም ይህንን መመለስ የሚችል እንደሆነ አንስተዋል።
በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ ወደብ ካላቸው ሀገራት ጋር በመነጋገር የወደብ ትራንስፖርት፤ የወደብ ልማት ፤የባሕር ትራንስፖርት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
ብሉ ኢኮኖሚ የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ነው።
ስትራቴጂው በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በዓሳ ሀብት ልማትና በሌሎች አካታችና ዘላቂ የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሀብቶች አጠቃቀምን ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።