ኢጋድ በቀጣናው ያሉ ሀገራት ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ምን አለ ?
ኢጋድ የኢትዮ-ሱዳን “የድንበር አከባቢ ውጥረት” የሀገራቱ መሪዎች የተጫወቱት ሚና የሚደነቅ መሆኑ ገለጸ
የኢጋድ ቃል አቀበይ ኑር መሃመድ ሼክ “አዲሱ የሶማሊያ መንግስት ሊታገዝ ይገባል” ብለዋል
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት(ኢጋድ) በቀጣናው ያሉ ሀገራት ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርቷል።
የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውጥረት
በቅርቡ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የድንበር ውጥረት ተባብሶ ሌላ ቀውስ እንዳይፈጥር ሀገራቱ የተፈጠረውን ውጥረት ከሚያባበስ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ እንዲታቀቡ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሲያሳስብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
ይህን ተከትሎ የሀገራቱ ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት መሰረት አሁን ላይ ተከስቶ ነበረውን ውጥረት ረገብ ማለቱ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁትና ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢጋድ ቃል አቀባይ ኑር መሃመድ ሼክ ሁለቱም ሀገራት የነበረውን ውጥረት ለማረጋጋት የሄዱበት ርቀት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ሁለቱንም ሀገራት በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ውጥረት ለመፍታት ኢጋድ የራሱን ሚና ቢጫወትም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ናቸው ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ሌ/ጀኔራል አልቡርሃን በኬንያ በነበረው የኢጋድ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የጎንዮሽ ውይይት ለተፈጠረው ችግር የሁለትዮሽ መፍትሄ በማበጀታቸው ውጥረቱን ሊረግብ ችሏል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሀገራትና እንደ ዉሃ የመሳሰሉ የጋራ የሆነ ተፈጥሮአዊ ሃብት የሚጋሩ ናቸው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አሁንም ቢሆን ሀገራቱ ለመልካም ጉርብትናቸው ቅድሚያ በመስጠት የተፈጠረውን ችግር በሰላመዊ መንገድ ለመፍታት የጀመሩት ጥረት ኢጋድ ያበረታታል ብሏል።
ደቡብ ሱዳን
ኢጋድ በቅረቡ ባወጣው መግለጫ፤ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለመተግበር ግልጽ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖራቸው ይገባል ሲል ማሳሰቡ የሚታወስ ነው፡፡
ኢጋድ የብሔራዊ አንድነት እና ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት የምርጫ አፈጻጸምን ጨምሮ ቀሪ ተግባራትን ለማጠናቀቅ ግልጽ የሆኑ መለኪያዎች ተጨባጭ የጊዜ ሰሌዳዎችን እና ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁም ጠይቆ ነበር።
ይህን ተከትሎም ሀገሪቱ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ የተመረጠ መንግስትን ለማምጣት የሚያስችል ፍኖተ ካርታን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ከቀናት በፊት ከፍኖተ ካርታው አዘጋጅ ኮሚቴ መቀበላቸው የሀገሪቱ የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል።
የኢጋድ ቃል አቀባዩ ኑር መሃመድ ሼክ የደቡብ ሱዳን እርምጃ የሚበረታታ ነው ብለውታል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2018 በደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች መካከል ለተደረሰው ስምምነት ኢጋድ ዋና አስተባበሪ እንደነበር ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የተደረሰውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እያሳዩት ያለውን ቁርጠኝነት የሚመሰገን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን መጻኢ እጣ ፈንታና ሰላም አውን የሚሆነው ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሪክ ማቻር እንዲሁም የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ከስምምነት የተደረሰባቸውን ቁልፍ ጉዳዮች ወደ ተግባር መቀየር ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ግን አልሸሸጉም ቃል አቀባዩ፡፡
ቃል አቀባዩ ኑር መሃመድ ሼክ “በሚቀጥለው አመት ምርጫ ማካሄድ፣ ህገ-መንግስት መቅረጽ እንዲሁም አሳታፊ በሆነ መልኩ የሀገሪቱ ጦር ማዋቀር አሁንም የደቡብ ሱዳን መሪዎች በስምምነቱ መሰረት እውን ሊያደርጓቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው”ም ብለዋል፡፡
ኬንያ
የኢጋድ ቃል አቀባይ ኬንያ ተጠባቂ ስለሆነው የኬንያ ምርጫም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኬንያ ምርጫ በማድረግ ረገድ ከነጻነቷ ማግስት ጀምሮ ጥሩ የሚባል ልምድ ያላትና የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካን በማስተዋወቅ በቀጣናው ቀዳሚ መሆኗን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ኢጋድ የኬንያ የምርጫ እና የድንበር ጉዳዮች ኮሚሽን ባቀረበለት ግብዣ መሰረት፤ ምርጫው እንደሚታዘብም ጭምር ተናግረዋል፡፡
“የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢጋድን ልዑክ እንዲመሩ በመመደባቸው ክብር ይሰማናል”ም ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ሶማሊያ
በቅርቡ በሶማሊያ የተካሄደውን ምርጫ እየተራዘመ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በተለያዩ ወቅቶች ስጋት አዘል መግለጫዎች ሲያወጣ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ባለፈው ታህሳስ ወር 2021 በኬንያ ሞምባሳ በተሳለጠው የኢጋድ ጉባኤ ላይ “ሶማሊያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያለች ሀገር ናት” ያሉበት ንግግር አይዘነጋም፡፡
እንደተሰጋው ሳይሆን ፤ ሶማሊያውያን ዴሞክራሲያዊ ነው የተባለለትን ምርጫ በማድረግ አዲስ ፕሬዝዳንት እስከሞሾም የደረሱበት የቅርብ ጊዜ አጋጣሚም የሚታወስ ነው፡፡
የሶማልያ ምርጫና ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት አስተያየታቸውን የሰነዘሩት የኢጋድ ቃል አቀባዩ ኑር መሃመድ ሼክ ሶማሊያውያን ታሪክ ሰርተዋል ብለዋል፡፡
ኢጋድ በሶማሊያ የተካሄደውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተከትሎ ወደ ስልጣን ለመጡት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድን እና ለሀገሪቱን ፓርላማ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በመላክ ቀዳሚው ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ፤ እንደወትሮ ሁሉ ኢጋድ ለሶማሊያ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅ መሆኑም አረጋግጠዋል፡፡
“አሁን በድጋሚ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የዳበረ የአመራር ክህሎት ያላቸው ሀገር መሪ ናቸው፡፡ አሁን ላይ የሶማሊያ ፌዴራል ግዛቶችን በማግኘት በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እያደረጉት ያለውን ጥረት እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ እየሰሩት ያለው ስራ የሚበረታታ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አልሻባብን በተመለከተ ሲናገሩም “አልሻባብ የሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ቀጠናው ስጋት ነው” ብለዋል፡፡
የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት ሶማሊያን እውን ለማደረግ ከአዲሱ ሶማሊያ መንግስትን በማገዝ ጋር በቅርበት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡