ከፍተኛ ነዳጅ ክምችት ባለቤቷ ደቡብ ሱዳን ለዓመታት በዘለቀው ግጭት የተጎዳውን ኢኮኖሚዋን ለማደስ እየሰራች ነው
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ደቡብ ሱዳንን ከአባልነት ማገዱን አስታወቀ፡፡
ኢጋድ ደቡብ ሱዳንን ያገደው በየዓመቱ ለተቋሙ መክፈል የሚጠበቅባትን መዋጮ ባለመክፈሏ እንደሆነም የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል።
የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ፣ የመገናኛ እና የፖስታ አገልግሎት ሚኒስትር ሚካኤል ማኩዌ ሀገራቸው በተባለው ምክንያት ከኢጋድ መታገዷ አረጋግጠዋል።
"መዋጮ ስላልከፈልን ብቻ ከኢጋድ ታግደናል፣ 14 ያህሉ የእኛ ኮታ የሆኑ የስራ ቦታዎች ቢኖሩም መዋጮችንን ለረጅም ጊዜ ስላልከፈልን ብቻ እነሱን ልንይዛቸው አልቻልንም” ብለዋል ሚኒሰትሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ማይክ አዪ ድንግ በካቢኔ ስብሰባው ላይ ለኢጋድ መዋጮ ሚሆን ገንዘብ መጠየቃቸውንም አስታውቀዋል።
"ካቢኔው በጥልቀት ከመከረ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እነዚህን ሁሉ ከአዲሱ የገንዘብ ሚኒስትር ጋር እንዲወያዩበት ተወስኗል፤ ይህም ሁሉንም ውዝፍ ለመክፈል የሚያስችል መንገድ የሚያመቻች ነው" ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል።
ባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ላይ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ /ኢጋድ/ ደቡብ ሱዳን አመታዊ መዋጮ እየከፈለች ስላልሆነ ከአባልነት ሊያግዳት እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።ከፍተኛ ነዳጅ ክምችት እንዳላት የሚነገርላት ደቡብ ሱዳን ከታህሳስ 2013 ጀምሮ ለዓመታት በዘለቀው ግጭት የተጎዳውን ኢኮኖሚዋን ለማደስ እየታገለች ትገኛለች።
የምስራቅ አፍሪካ የንግድ እና የጸጥታ ቡድን የሆነው ኢጋድ በ1986 የተመሰረተ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳን በአባልነት ያቀፈ ነው።