በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር ከሳምንት ሳምንት በ43 በመቶ እየጨመረ ነው
ባለፈው ወር ብቻ ተጨማሪ 1 ሚሊዬን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል
የቫይረሱ ስርጭት ለተከታታይ ስምንት ሳምንታት እንዳሻቀበ መቀጠሉን ተከትሎ የአህጉሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዬን አሻቅቧል
በአፍሪካ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር ከሳምንት ሳምንት የ43 በመቶ ጭማሪ እያሳየ ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ለቁጥሩ መጨመር የድንገተኛ ህክምና መስጫ አልጋዎች እና የኦክስጅን እጥረትን በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡
በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል ያለው የሞት ምጣኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ከፍ ያለ እንደሆነም ነው የድርጅቱ መግለጫ የሚያመለክተው፡፡
የቫይረሱ የሞት ምጣኔ በዓለም 2.2 በመቶ ነው፡፡ በአፍሪካ ግን 2.6 በመቶ ይደርሳል፡፡
ለ3ኛ ጊዜ ያገረሸው የቫይረሱ ስርጭት ብዙዎችን እየገደለ እንደሆነም ነው የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር የተናገሩት፡፡
ለዚህ ደግሞ ‘ዴልታ’ የተሰኘው የቫይረሱ ዝርያ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
ከፍተኛ የመሰራጨት አቅም ያለው ‘ዴልታ’ በ21 የአህጉሪቱ ሃገራት ተንሰራፍቷል፡፡ ‘አልፋ’ በ35 ፣‘ቤታ’ ደግሞ በ20 ሃገራትም ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት 6 ሺ 294 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ይህ ቀደማ ካለው ሳምንት ከነበረው የሟቾች ቁጥር (4 ሺ 384) የጨመረ ነው፡፡
ናሚቢያ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ቱኒዚያ ፣ ኡጋንዳ እና ዛምቢያ ከፍተኛ የሟቾች ድርሻን (83 በመቶ) ይይዛሉ፡፡
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለስምንት ተከታታይ ሳምንታት አሻቅቧል፡፡ ይህም አጠቃላይ የአህጉሪቱን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዬን ከፍ አድርጎታል፡፡ ባለፈው ወር ብቻ ተጨማሪ 1 ሚሊዬን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህ እጅግ አጭር ጊዜ ነው፡፡ ከ4 ወደ 5 ሚሊዬን ለመግባት ዘለግ ያሉ ወራትን ወስዶ ነበር፡፡
ይህ በአህጉሪቱ እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተከትቦ በሚገኝበት ሁኔታ ነው የሆነው፡፡ እስካሁን 52 ሚሊዬን ህዝብ ብቻ ነው የተከተበው፡፡ ይህም በመላው ዓለም ከተከተበው 3.5 ቢሊዬን ህዝብ ውስጥ የ1.6 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ከ52 ሚሊዬኑ 18 ሚሊዬኑ ብቻ ናቸው ሙሉ ክትባቱን ያገኙ፡፡
የክትባቶች አቅርቦት በመጪዎቹ ሳምንታት ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ እስከ መጪው መስከረም ድረስ ለ10 በመቶ ያህሉ የአህጉሪቱ ህዝብ ሙሉ ክትባት ለመስጠት 190 ሚሊዬን፣እስከ ጥር ድረስ 30 በመቶ ያህሉን በሙሉ ለመከተብ ደግሞ 750 ሚሊዬን ተጨማሪ ክትባቶች ያስፈልጋሉ እንደ ድርጅቱ ገለጻ፡፡
ሁኔታው በኢትዮጵያ ጭምር ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ያስታወቀው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቫይረሱ መከላከያ መንገዶች በአግባቡ እንዲተገበሩ አሳስቧል።