በኮሮና ቫይረስ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ተመድ ጠየቀ
600 ሚሊየን የሚደርሱ ተማሪዎች ትምህርታቸዉ አደጋ ላይ መሆኑ የተመድ መረጃ ያመለክታል
ከት/ቤቶች በፊት መጠጥ ቤቶችን እና ሌሎች አገልግሎቶች መጀመራቸው “አስከፊ ስህተት” ነበር ተብሏል
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች በድጋሚ እንዲከፈቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕፃናት ፈንድ ጥሪ አቀረበ።
ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሆኖ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባለ መረጃ 600 ሚሊየን የሚደርሱ ተማሪዎች ትምህርታቸዉ አደጋ ላይ መሆኑንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ቃል አቀባይ ጄምስ ኤሌደር “መንግስታት የኮሮና ቫይረስ ቀውስ እና የበሽታውን ስርጭት ሊያጋጥማቸው የሚችለዉን ችግር በማሰብ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ከባድ ዉሳኔ መሆኑን እንገነዘባለን፤ ይህ ሊቀጥል አይችልም” ሲሉ በጀኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግሯል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለመዝጋት የመንግስታት የመጀመሪያ ዉሳኔ እንደነበር ሁሉ በድጋሚ መክፈትም የመጀመሪያ ዉሳኔያቸዉ መሆን ይገባዉ ነበር ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ከትምህርት ቤቶች በፊት መጠጥ ቤቶችን እና ሌሎች አገልግሎቶች መጀመራቸው “አስከፊ ስህተት” ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ መግለፃቸውም የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘግቧል፡፡
ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ሁሉም መምህራንና ተማሪዎች ክትባት እስኪወስዱ መጠበቅ አይቻልም ያሉት ጄምስ ኤሌደር ወረርሽኙ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ችግር ቢኖርም መንግስታት የትምህርት በጀታቸውን ጠብቀዉ እንዲቆዩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ትምህርት በኦላን እየሰጡ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው፡፡