መንግስት የከፍተኛ ትምህርትን በነጻ መስጠት ሊያቆም ነው፡፡
መንግስት ለዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ሲያደርግ የቆየውን የወጪ መጋራት (cost sharing) አሰራር ሊያስቀር መሆኑን አስታወቀ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወ/ማርያም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት
ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደ ስብሰባ ላይ እንዳሉት፣ መንግስት ለዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የነጻ ትምህርት አድል ማመቻቸቱ አሁን በየተቋማቱ ለሚከሰቱ ግጭቶች አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም ተማሪዎች ለግጭቶች ተባባሪ እየሆኑ በመሆናቸው፣ መንግስት የወጪ መጋራት በሚል እያቀረበው ያለውን አገልግሎት ማቋረጥ ፈልጓል ብለዋል።
በመሆኑም ከፍለው መማር የማይችሉና ሌሎች የማህበራዊ ችግሮች ካሉባቸው ተማሪዎች ውጭ፣ የከፍተኛ ትምህርት ከዚህ በኋላ በነጻ ስለማይሰጥ መንግስት የወጪ መጋራትን የሚተካ አሰራር ያዘጋጃል ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
በቀጣይ ማንኛውም ተማሪ ከፍሎ ወይም በብድር እንዲማር እንደሚደረግም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ይሁንና መንግስት መቼ ላይ የወጪ መጋራት አገልግሎትን እንደሚያቋርጥ እስካሁን አለመወሰኑን ፕሮፌሰር ሒሩት ወ/ማርያም ተናግረዋል።