ኢትዮጵያ የመንግስት ሰራተኞቿን ብቃት ልትመዝን ነው
ምዘናውን በግል መስጠት የሚፈልጉ ተቋማት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር መዋዋል እንደሚችሉም ተገልጿል
ምዘናው ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች ይሰጣል ተብሏል
ኢትዮጵያ የመንግስት ሰራተኞቿን ብቃት ልትመዝን እንደሆነ አስታወቀች፡፡
የሰራተኞቹ ብቃት ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ ይመዘናል የብቃት ማረጋገጫም ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምዘናው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚዘጋጅ ነው ያሉት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ በዛብህ ገብረየስ ምዘናው ብቁና ተወዳዳሪ ሠራተኛ ለማፍራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ምዘናው ለሁሉም የመንግስት ተቋማት እንዲያገለግል የጋራ መስፈርት ወጥቶለት መዘጋጀቱንም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
የብቃት ምዘናውን ወደ መንግስት ተቋማት ለሚገቡ አዲስ ሠራተኞችም ሆነ ለነባሮቹ ለመስጠት ከታሰበው ጊዜ በላይ የወሰደ በቂ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አቶ በዛብህ ገልጸዋል።
ስለምዘናው የነበሩ ብዥታዎችን የማጥራትና ምዘናው የሚካሄድበትን ቦታ እና ሁኔታ የማመቻቸት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በመሆኑም ምዘናው ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ ይሰጣል ነው ያሉት።
በአንዳንድ ተቋማት ሲሰጥ የቆየው የብቃት ምዘና በአዲሱ የምዘና መስፈርት የሚካተት እንደሚሆንና ምዘናውን በግል መስጠት የሚፈልጉ ተቋማትም ከኮሚሽኑ ጋር መዋዋል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
እንደ ኮሚሽነር በዛብህ ገለጻ በቀጣዮቹ ዓመታት የመንግስት ተቋማት የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች በጥልቀት ይፈተሻሉ።
ተመሳሳይ ስራና ዓላማ ይዘው የሚሰሩ ተቋማት ወደ አንድ የሚመጡበት ሁኔታም ይኖራል።
በተለይም ከምርጫው በኋላ የመንግስት ተቋማትን አወቃቀር ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሲቪል ሰርቪሱን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ይታወቃል።