ወረርሽኙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሚኒስትሯ ጥሪ አቀረቡ
እስካሳለፍነው ቅዳሜ ብቻ በነበሩ 10 ቀናት ከ12 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ የ149 ሰዎች ህይወት አልፏል
ዶ/ር ሊያ በወረርሽኙ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ባሳለፍነው ሳምንት መመዝገቡን ተናግረዋል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የወረርሽኙን ወቅታዊ ሃገራዊ የስርጭት ሁኔታ በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሯ ስርጭቱ ባለፉት ወራት በተለይም ባለፉት ሳምንታት እጅግ መጨመሩን አስታውቀዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት ከጀመረበት ከዛሬ ዓመት ጀምሮ የስርጭት ምጣኔው፣ በቀን የሚያዙ እና በጽኑ የሚታመሙ እንዲሁም የሚሞቱ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ባሳለፍነው ሳምንት መመዝገቡንም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡
እንደ ዶ/ር ሊያ ገለጻ በመቶኛ ከ10 በታች የነበረው በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር አሁን በአማካይ 17 በመቶ ወይም ከመቶው 17 ሰው ወደመገኘት አሻቅቧል፡፡
እስካሳለፍነው ቅዳሜ ብቻ በነበሩ 10 ቀናት ከ12 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ የ149 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ የሞት ምጣኔው ቀደም ባለው ሳምንት 123 ነበር፡፡
የጽኑ ታማሚዎች ቁጥርም በነዚሁ ቀናት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ450 በልጧል፡፡
የጽኑ ህሙማን ክፍሎች መሙላት፣ የመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር) መያዝ እና የኦክስጅን እጥረቶች ማጋጠማቸውንም ነው ዶ/ር ሊያ የተናገሩት፡፡
ይህን ለሚመለከታቸው አካላት እያሳወቅን እንገኛለን ያሉም ሲሆን በመከላከል ስራዎች ላይ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን የሚያስጨንቅ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ወረርሽኙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ሁሉም አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህበረሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ጥንቃቄውን ሊያጠናክር፣በትራንስፖርት አካባቢ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እና የእምነት ተቋማትም ኃላፊነቱን ወስደው ህዝቡን ከወረርሽኙ ሊታደጉ እንደሚገባም አሳበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ ያስገባችውን የአስትራ ዜኔካ ክትባት መስጠቷን እንደምትቀጥልም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
አንዳንድ የአውሮፓ ሃገራት ክትባቱ የደም መርጋትን ያስከትላል በሚል ለዜጎቻቸው መስጠት አቁመዋል መባሉ የሚታወስ ነው፤ ምንም እንኳን የዓለም ጤና ድርጅት የሚባለው ያልተረጋገጠ ነገር እንደሆነና መሰጠቱ እንዲቀጥል ቢያሳስብም፡፡