ኢትዮጵያ በ30 ደቂቃ ውስጥ ኮሮና ቫይረስን መመርመር የሚያስችሉ 70 ማዕከላትን ልትከፍት ነው
ከ70ዎቹ ዘመናዊ መመርመሪያ ማዕከላት ውስጥ 10ሩ በትግራይ ክልል ይቋቋማሉ ብለዋል ዳይሬክተሩ
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በስራ ላይ ያሉት የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያዎች ቫይረሱን ለመለየት ከ4 እስከ 7 ሰዓት ይፈጅባቸዋል
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአሁን ሰዓት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አገልግሎት በ77 ማዕከላት እየተሰጠ መሆኑን ገልጿል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የላብራቶሪ አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ከበደ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናሩት ከ77ቱ የምርመራ ማዕከላት ውስጥ በትግራይ ክልል ከነበሩት 6 ማዕከላት በመቀሌ ካለው ውጪ አምስቱ አሁን ላይ ከአገልግሎት ውጪ ናቸው፡፡
አቶ አዲሱ ቫይረሱን ከ4 አስከ 7 ሰዓት ውስጥ መለየት ከሚያስችሉ 77 የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከላት ተጨማሪ 8 የምርመራ ማዕከላት እንደሚከፈቱም ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በፍጥነት እየተሰራጨ በመሆኑ የምርመራ አቅምን ማሳደግ የግድ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ ያሉት የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያዎች ቫይረሱን ለመለየት ከ4 እስከ 7 ሰዓት ይፈጅባቸዋል።በዚህም መሰረት በስራ ላይ ያሉት እንዳሉ ሆነው ተጨማሪ ዘመናዊ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያዎችን መጠቀም የግድ ነው ብለዋል አቶ አዲሱ።
በመሆኑም ቫይረሱን በ30 ደቂቃ ውስጥ መመርመር የሚያስችሉ 70 የምርመራ ማዕከላትን በማቋቋም ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።ለምርመራ ማዕከላቱ የሚያስፈልጉ ማሽኖች እና ሌሎች አጋዥ መሳሪያዎች ከውጭ አገራት በመግባት ላይ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል።
ከ70ዎቹ ዘመናዊ መመርመሪያ ማዕከላት ውስጥ 10ሩ በትግራይ ክልል እንደሚደረጉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመሩንና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የኮሮና ጽኑ ህሙማን ቁጥርም አሻቅቧል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ኢኒስቲትዩቱ በኢትዮጵያም በኮቪድ 19 ቫይረስ የመሰራጨት አቅሙን ጨምሮ አስጊ በሆነ ደረጃ በ12.80 በመቶ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ጨምሯል የሚል መረጃ አውጥቶ ነበር፡፡
ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መግባቱ የተረጋገጠው መጋቢት 4፣2012ዓ.ም ሲሆን በወቅቱም ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ከቡርኮና ፋሶ የመጣ ጃፓናዊ ዜጋ ላይ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን 2 ሚሊዮን 256ሺ 439 ሰዎች ላይ የኮሮና ምርምራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 181ሺ 869 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ 2ሺ 602 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ክትባቱ በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባና በክልሎች መሰጠት ተጀምሯል፡፡ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር 2.2 ሚሊዮን ክትባት በህንዱ ሴረም ኢኒስትቲዩት የተመረተ ክትባት መረከቧ ይታወሳል፡፡