8 የኮሮና ታማሚዎች በኦክስጂን እጥረት መሞታቸውን ተከትሎ የጆርዳን የጤና ሚኒስትር ስልጣን ለቀቁ
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሽር ሀኒ አልከሳዊና በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ምርመራ እንዲካሄድ ትእዛዝ ሰጥተዋል
ሚኒስትሩ ከወር በፊት በተደረገ የካቢኔ ሹም ሽር ነበር ወደ ስልጣን የመጡት
የጆርዳን የጤና ሚኒስትር ነዚር ሙፍሊሕ ኡበይዳት ከስልጣን ለቀቁ፡፡
ሚኒስትሩ ስልጣን የለቀቁት ዛሬ ስምንት የሚሆኑ የኮቪድ-19 ታማሚዎች፤ በኦክስጅን እጥረት ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ እንደሆነ ነው የሀገሪቱ ሚድያ የገለጸው፡፡
የቫይረሱ ታማሚዎች ሞት በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኦማን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ‘ሳልት ጠቅላላ ሆስፒታል’ የተከሰተ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር በሽር ሀኒ አል ከሳዊና የተፈጠረውን አሳዛኝ የዜጎች ሞት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ገለልተኛ ምርምራ እንዲካሄድ አዘዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለተፈጠረው ችግር የሚጠየቁ አካላት ይኖራሉ” ማለታቸውንም አል-ማምለካ የተሰኘው የሀገሪቱ የቴሌቭዝን ጣቢያ ዘግቧል፡፡
አል-ማምለካ የጤና ሚኒስትሩ ነዚር ሙፍሊሕ ኡበይዳት ከሀላፊነት መልቀቅ ከዚህ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ከወር በፊት በተደረገ የካቢኔ ሹም ሽር ነበር ወደ ስልጣን የመጡት፡፡
በጆርዳናውያን ዘንድ ትልቅ ድንጋጤን የፈጠረው ይክ ከስተት የሀገሪቱ ንጉስ ዳግማዊ አብደላ እና ልዑል አልጋወራሹ በሆስፒታሉ ያልተጠበቀ ጉብኝት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡
ንጉሱ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ወዲያውኑ እንዲሰናበቱ መዘዛቸውን የልዑላውያኑን ውሎ የሚከታተሉ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ኡበይዳት ስልጣን እንዲለቁ ያለሉት ንጉሱ ናቸውም ተብሏል፡፡
በጆርዳን እስካሁን 464 ሺ 856 ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 5 ሺ 244 ያህሉ ጽኑ ህክምና የሚሹ ናቸው፡፡