በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በ29 በመቶ ጨምሯል
የኮሮና ክትባት ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች መስጠት ቢጀመርም የጥንቃቄ ጉድለት ከፍተኛ ስጋት ነው
በሳምንቱ የኮሮና ሟቾች ቁጥር በ23.7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ድፍን አንድ ዓመት የሞላው የኮሮና ቫይረስ እስካሁን በኢትዮጵያ 159 ሺህ 72 ሰዎችን አጥቅቶ 2 ሺህ 365 ሰዎችን ደግሞ ገድሏል።
ቫይረሱ በገባበት ሰሞን የሕብረተሰቡ ጥንቃቄ መልካም የነበረ በመሆኑ በተፈራው ልክ ሰዎችን ሳያጠቃ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ በተጠናቀቀው ሳምንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር በ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ 9 ሺህ 25 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 120 ሰዎች ደግሞ ሀይወታቸው አልፏል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ያለውን ሪፖርት ስናየው ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 6 ሺህ 976 ሲሆን 97 ሰዎች ደግሞ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ይህም ቫይረሱ በኢትዮጵያ በመስፋፋት ላይ ሲሆን የቫይረሱ ስርጭት በ29 በመቶ የሟቾች ቁጠር ደግሞ በ23.7 በመቶ መጨመሩን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መስጠት የጀመረች ሲሆን በቅድሚያም የጤና ባለሙያዎች ፣ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች እና አመራሮች ይከተባሉ፡፡ በቀጣይም አዛውንቶች እና የጸጥታ ሀይሎቸ እንደሚከተቡ ይጠበቃል።
በአፍሪካ ካሉ 55 አገራት ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ግብጽ እና ኢትዮጵያ በተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚ አገራት እንደሆኑ የአፍሪካ በሽታዎች መካላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (CDC) በሪፖርቱ ገልጿል።
በደቡብ አፍሪካ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ሲያጡ ግብጽ እና ሞሮኮ ደግሞ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎችን የያዙ አገራት ናቸው።