የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ክትባቱን አስጀምረዋል
በትግራይ ክልል የኮሮና ክትባቶችን መስጠት ተጀመረ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተገኙበት በመቀሌ ጠቅላላ ሆስፒታል በተካሄደ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ነው ክትባቱ በይፋ መሰጠት የተጀመረው፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)ም በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ነበሩ፡፡
ዶ/ር ሊያ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች፣ እድሜያቸው ከፍ ያሉ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመጀመሪያው ዙር ክትባቱን በቀዳሚነት እንደሚያገኙ በመርሐ ግብሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ የክትባቱ አቅርቦት በአለም አቀፍ ደረጃ ውስንነት እንዳለበት የገለጹም ሲሆን ህብረተሰቡ በክትባቱ እንዳይዘናጋ እና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉ በበኩላቸው የመርሃ ግብሩ መጀመር ያለንበትን ችግር በመቋቋም ቫይረሱ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ለማጠናከር በሚኒስቴሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፤ ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ያሳሰቡት ዶ/ር ሙሉ፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ጠንክረው እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ፋሲካ አምደስላሴ ናቸው፡፡
ዶ/ር ፋሲካ መርሃ ግብሩ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት በክልሉ ይተገበራል ብለዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ዛሬ በመላ ሃገሪቱ ነው የተጀመረው፡፡ በአዲስ አበባ የጤና ሚኒስቴር ዴዔታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በተገኙበት ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል መጀመሩን አል ዐይን በስፍራው ተገኝቶ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው እሁድ 2 ነጥብ 2 ሚሊዬን የአስትራዜኔካ የኮሮና ክትባቶችን መቀበሏም ይታወሳል፡፡ እስከ መጭው ታህሳስ 2014 ዓ.ም ድረስ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ 20 በመቶ ያህሉን ለመከተብ ታቅዷል መባሉም አይዘነጋም፡፡