ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ውስጥ ተካታለች
ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ውጪ ሀገራት መላኳን ገለጸች።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አንደገለጸው ባለፉት ስድስት ወራት 123 ነጥብ 6 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ ሀገራት ለመላክ ታቅዶ 148 ነጥብ 8 ሺህ ቶን ቡና ተልኳል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለአል ዐይን እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጪ ሀገራት ከሚላክ ቡና 405 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 578 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ274 ሚሊየን ዶላር ወይም በ60 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል።
በተጠቀሱት ወራት ወደ ውጭ ሀገራት የተላከው ቡና እና የተገኘው ገቢ በኢትዮጵያ የቡና ንግድ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑንም አቶ ሻፊ ተናግረዋል።
ጀርመን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ቤልጂየም፣ ጃፓን እና አሜሪካ የኢትዮጵያ ቡና በብዛት ከተላከባቸው አገራት መካከል ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ ቻይና ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ቡና በመቀበል ረገድ 33ኛ ደረጃ ላይ ከነበረችበት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ስምንተኛ ደረጃ መጥታለች ተብሏል።
በቡና ንግዱ ላይ የኮሮና ቫይረስ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ቀጥታ ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ ስጋት ቢቀመጥም ምንም አይነት ተጽዕኖ እንዳላሳደሩም አቶ ሻፊ ኡመር ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ በቡና አቅራቢ እና ላኪ መካከል የነበረውን የተንዛዛ አስራር በማሳጠር፣ ከዚህ በፊት በቡና ድለላ ላይ የነበሩ አሰራሮችን በማስወገዱ፣ የቡና ምርት ጥራት የሚያሳድጉ አሰራሮችን በመከተሉ፣ የግብይት ስርዓትን የሚያዘምኑ የበይነ መረብ ግብይቶችን በመከተሉ ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ የተሸለ ገቢ እንድታገኝ ያስቻሉ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸውም ብሏል።
አሁንም ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ ማግኘት ያለባትን ገቢ እያገኘት አይደለም የሚሉት አቶ ሻፊ ሩሲያ እና የምስራቅ እስያ ሀገራት ቡናችንን ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት ላይ በመሆናቸው እነዚህን ሀገራት በሰፊው እንጠቀማለንም ብለዋል።
ባለስልጣኑ የቡና ጥራትን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የበይነ መረብ ግብይትን የበለጠ ማዘመን፣ የቡና ጥራት ስልጠና ማዕከላትን ማስፋፋት፣ ከዩንቨርሲቲዎች ጋር በመነጋገር በቡና ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ባለሙያዎችን ማፍራት እና ቡና አምራች ክልሎችን ማብዛት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
ኦሮሚያ፣ ደቡብ ፣ሲዳማ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልለ ጋር የሚዋሰኑ እና በሶማሌ ክልል ስር ያሉ ወረዳዎች ቡና በማምረት ላይ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ሰምተናል።