በአንድ ሲኒ 928 ሚሊ ግራም ካፌይን ያለው የዓለማችን በጣም ጠንካራው ቡና…
ቡናው በመደበኛነት ከምንጠጣው 4 እጥፍ የበለጠ የካፌይን ይዘት አለው ተብሏል
“ባዮሃዛርድ” የተባለው ቡና በጣም አደገኛው መጠጥ ነው የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል
ባዮሃዛርድ ቡና በዓለም ላይ ካሉት ቡናዎች ሁሉ በጣም ጠንካራው ቡና የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
በፈረንጆቹ 2016 የተመሰረተው ባዩሃዛርድ ቡና ራሱን” ገንዘብ መግዛት የሚችለው የዓለማችን ጠንካራው ቡና” በሚል የተቋቋመ ሲሆን፤ ለመጠጣት ደህንነቱ የተጠበቀ እና ከፍተኛ መጠን ካፌይን ያለው ቡና ነው ተብሎለታል።
ባዮሃዛርድ ቡና በአንድ ሲኒ ቡና ውስጥ 928 ሚሊ ግራም ካፌይን ያለው ሲሆን፤ ይህም በቀን ከሚመከረው 400 ሚሊ ግራም የካፌይን መጠን ከእጥፍ በላይ የሆነ እና በጥንካሬው እና በኃይል ሰጪነቱ ከአብዛኞቹ የኃይል ሰጪ መጠጦች የሚበልጥ ነው።
ሰውነታቸው ካፌይንን መቋቋም ለማይችሉ ሰዎች 928 ሚሊ ግራም ካፌይን ያለውን ቡና መጠጣት በጣም አደገኛ መሆኑ ተነግሯል።
የባዮሃዛርድ ቡና መስራች ከሆኑት አንዱ የሆነው ዮናታን ፒንሃሶቭ የዓለማችን ጠንካራ ቡና ስለመፍጠር ሲናገር፤ “ለረጅም ቀን በስራ እና በትምህርት ለሚያሳልፉ ሰዎች ጥሩ ጉልበትያስፈልጋል፤ ይህንን ለማግኘት ደግሞ በርካታ ሲኒ ቡና ደጋግሞ መጠጣት የግድ ይላል፤ ስለዚህ የተለያየ ጣእም ያለው ቡና ስንጠጣ ከመዋል አንድ ጠንካራ ቡና የመፍጠር ሃሳብ መጣ” ብሏል።
በተለይም ለስራ ፈጣሪዎች፣ ቀናቸው ለሚረዝምባቸው ወላጆች፣ 18 ሰዓታትን በስራ ለሚያሳልፉ ሰዎች፣ ለተማሪዎች ነቃ ብሎ ለመቆየት ቡናው ጠቃሚ እንደሆነም ነው ዮናታን የተናገረው።
በቡናው ማሸጊያ ጀርባ ላይ የተጻፈው የማስጠንቀቂያ መልዕክትም፤ “በአንድ ሲኒ 928 ሚሊ ግራም ካፌይን የያዘው ቡና ባሬስታችሁ ከሚያቀርብላችሁ ቡና በአራት እጥፍ የበለጠ ነው” ይላል።
ይህ ቡና ከመጠን በላይ ምርታማ እንድትሆኑ፣ ምሸትን ንቅት ብለው እንዲያሳልፉ እና የአልበገሬነት ስሜት እንዲሰማዎ ያደርጋል የሚል ማስታወቂያም በቡናው መሸጊያ ላይ ተጽፏል።
ባዮሃዛርድ ቡና በመልእክቱ ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን እና የጥንቃቄ ሂደቶችን በመከተል ቡናዬን መጠጣት ትችላላችሁ ብሏል።
ጠንካራው ቡና ልብ ድካም ላለባቸው ሰዎች እንደማይሆንም ባዮ ሃዛርድ አስጠንቅቋል።