በኢትዮጵያ 20 ሚሊየን ዜጎችን የኮቪድ-19 ክትባት ለመከተብ ያለመ ዘመቻ ነገ ይጀመራል
በቀጣዮቹ 2 ሳምንታት በሚካሄደው ዘመቻ ክትባቱ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ይሰጣል
እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑ ደግሞ የፋይዘር ክትባት እንደሚሰጥም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
በኢትዮጵያ 20 ሚሊየን ዜጎችን የኮቪድ-19 ክትባት ለመከተብ ያለመ ዘመቻ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የክትባት ዘመቻውን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፤ መንግስት በተከታታይ ክትባቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እስካሁን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ክትባቶችን ለህብረተሰቡ መስጠቱን ገልፀዋል።
ሆኖም ግን በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ ከታለመው አንፃር እና ሀገሪቱ ካላት የህዝብ ቁጥር አንፃር አፈጸጸሙ አነስተኛ በመሆኑ የዘመቻ ስራውን ማከናወን አስፈልጓል ማታውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመሆኑም የኮቪድ-19 ክትባቱን በአጭር ጊዜ ለታላሚው ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ለሚቀጥሉት 2 ሳምንታት እና ከዚያ በላይ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች በዘመቻ መልክ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ዶ/ር ሊያ አክለውም፤ ካሁን ቀደም እየተሰጡ ካሉት የአስትራዜኒካ፣ ስይኖፋርማ እና ጄ ኤንድ ጄ ክትባቶች በተጨማሪ የፋይዘር ክትባት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።
የፋይዘር ክትባቱንም ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆናቸው ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንዲሁም ስርጭቱ ወደ ክልሎች እየተደረገ ስለሆነ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በክልሎች መሰጠት እንደሚጀምር አስረድተዋል።
ዶ/ር ሊያ አክውም አሁን ላይ ከ8 ሚሊየን በላይ ክትባት (ዶዝ) በእጅ የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ተጨማሪ ክትባቶች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ በመሆኑ በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ዜጎችን በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 የመከላከሉን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በክትባቱ ዙሪያ የሚወሩ የተሳሳቱ አመለካከቶችን፣ አሉባልታዎችንና ኢሳይንሳዊ የሆኑ መረጃዎችን ወደ ጎን በመተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራታቸው የተረጋገጠ ክትባቶችን በመውሰድ ጤንነቱን መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል።
የኮቪድ-19 በሽታ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት 368 ሺ 979 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን 6 ሺህ 630 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ህይወታቸው አልፏል።