ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለመንግስት ሰራተኞች አስገዳጅ ለማድረግ አስባለች?
ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ከትባትን በሚፈለገው ልክ እየተከተቡ አለመሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
የኮሮና ቫይረስ ከትባትን የወሰደ ሰው ካልተከተበ ሰው ጋር ሲነጻጸር በ11 በመቶ የመሞት እድል አለው
ወደ ኢትዮጵያ ከገባ 18 ወራት የሆነው ኮሮና ቨይረስ እስከ ትናንት ድረስ ከ5 ሺህ በላይ ዜጎችን ህይወት ሲቀጥፍ፤ ከ335 ሺህ በላይ ሰዎችን አጥቅቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የቫይረሱ ስርጭት መጠን እና የሞት ምጣኔው በፍጥነት እየጨመረ ነው ብለዋል።
- ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መስጠቷን ገለጸች
- ኢትዮጵያ በቀጣይ 2 ወራት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዶዝ የኮሮና ክትባት እንደምታገኝ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በግዢ እና በእርዳታ እስካሁን ከ6 ሚሊየን በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባቷን እና ግማሹ ክትባት መሰጠቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ይሁንና ይህ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መጠን በጥቂት ቀናት ወስጥ ሊያልቅ የሚችል ቢሆንም ህብረተሰቡ ክትባቱን በሚፈለገው መጠን እየወሰደ አይደለም ብለዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ዜጎችን እንዲጨምር እያደረገ በመሆኑ ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ከትባቶችን እንዲወሰድ ዶክተር ሊያ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫው ላይ በአሜሪካ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል ወይም ሲዲሲ ባሳለፍነው ሳምንት 600 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበትን ጥናት ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት ያልተከተቡ ሰዎች፣ ከተከተቡት ጋር ሲነጻጸሩ በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው፣ ከ4.5 እጥፍ በላይ ነው፤ሆስፒታል የመግባት እድላቸው ደግሞ ከ10 እጥፍ በላይ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ያልተከተቡ ሰዎች ከተከተቡት ጋር ሲነጻጸሩ በቫይረሱ ተጠቅተው ታመው የመሞት እድላቸው ከ11 እጥፍ በላይ መሆኑንም ሚኒስትሯ ጥናቱን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በርካታ የዓለማችን ሀገራት በተለይም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞች በግድ ክትባቱን እንዲወስዱ እያደረጉ ነውና ኢትዮጵያስ ወደዚህ ውሳኔ ልትገባ ትችላለች? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
“ብዙ ሀገራት ክትባቶችን አስገዳጅ ማድረግ ጀምረዋል በተለይም በተወሰኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የግድ አድርገዋል።እኛም እያየን ነው ያለነው ከሳይንቲፊክ አድቫዘሪዎቻችን ጋር እየተነጋገርንበት ነው” ብለዋ።
“የጤና ባለሙያዎችን እና የሌሎች ተጋላጭ ተቋማት ሰራተኞች ከስራ ባህሪያቸው አንጻር ቅድሚያ ክትባቱን እንዲወስዱ ተደርጓል፤ይሁንና ሁሉም ክትባቱን አልወሰዱም። እነዚህ አካላት አሁንም ክትባቱን እንዲወስዱ በጥብቅ አሳስባለሁ” ያሉ ሲሆን፤ “በቀጣይ በምን መልኩ ነው አስገዳጅ የምናደርገው የሚለውን ነገር እንደ አገር በማየት ላይ ነን። በቀጣይ አዲስ ነገር ካለ እናሳውቃለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን በ15 ከተሞች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ወይም ማስክ አጠቃቀም ምን እንደሚመስል ጥናት ማድረጉም በመግለጫው ላይ የተነሳ ሀሳብ ነበር።
በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ እስከ 83 በመቶ ደርሶ የነበረው የማስክ አጠቃቀም በአሁኑ ሰዓት 52 በመቶ ሲሆን በሌሎች ከተማዎች አማካዩ 16 በመቶ ነው። በአንዳንድ ከተማዎች ደግሞ ከ5 በመቶ በታች እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ትምህርት ቤቶች በመከፈት ላይ መሆናቸው፤ ልዩ ልዩ በአላት የሚከበሩ መሆኑ ፤የተማሪዎች ምረቃ በመካሄድ ላይ መሆናቸው እና ሌሎች ማህበራዊ ክንውኖች የቫይረሱን ሰርጭት ሊጨምረው እንደሚችል ሚኒስቴሩ ስጋቱን ገልጿል።