ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መስጠቷን ገለጸች
በሕንድ ያለው የኮሮና ስርጭት ኢትዮጵያ ለማግኘት ያሰበችውን ተጨማሪ ክትባት እንደማያስተጓጉል ተገልጿል
ተጨማሪ 530 አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ ያላቸው አልጋዎችን ለመግዛት መንግስት በሂደት ላይ ነው
ኢትዮጵያ የአስተራ ዜኒካ እና የሲኖ ፋርም ምርቶች የሆኑ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በመስጠት ላይ ትገኛለች።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን እሸቱ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ክትባቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዜጎች በመሰጠት ላይ ነው።
እስከ ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለ 1 ሚሊዮን 682 ሺህ 108 ዜጎች የአስተራ ዜኒካ ክትባት ሲሰጥ ለ 2 ሺህ 342 ዜጎች ደግሞ የሲኖ ፋርም ምርት ክትባት ተሰጥቷል ተብሏል።
እንደ ሀገር በኢትዮጵያ በድምሩ ለ1 ሚሊዮን 684 ሺህ 450 ሰዎች ክትባት መሰጠቱ ተገልጿል።
እስካሁን በነበረው የክትባት ሂደት ውስጥ ያጋጠመ ችግር የለም ያሉት ዶክተር ወንድወሰን መጀመሪያ ላይ አጋጥሞ የነበረው ክትባቱን የመውሰድ ፍላጎት መቀነስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተካከለ መምጣቱንም ጨምረው ገልጸዋል።
በሕንድ ያለው አሁናዊ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጠን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለማግኘት ያሰበችውን ተጨማሪ ክትባት አያስተጓጉለውም ብለዋል።
ተጨማሪ ክትባቶችን በግዢ እና በእርዳታ ከአስትራ ዜኒካ ፣ ከሲኖ ፋርም እና ከሌሎች መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ለማግኘት ድርድር በመካሄድ ላይ መሆኑንም ዶክተር ወንድወሰን ተናግረዋል።
አሁን ላይ እየወጣ ባለው እለታዊ የኮቪድ 19 ሪፖርት ፣ በቫይረሱ እየተጠቁ እና ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ዜጎች ቁጥር ከአንድ ወር በፊት ከነበረው አንጻር መቀነስ እያሳየ ነው፡፡ ይህ ማለት የቫይረሱ ስርጭት መቀነሱን ያሳያል ወይ? በሚል ላንሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡ “ዕለታዊ አሀዙ ከአንድ ወር በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ የመጣ ቢመስልም ይህ ሪፖርት እውነታውን አያሳይም” ሲሉ ተናግረዋል።
“አሁን ላይ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እየተካሄደ ያለው ወደ ህክምና ተቋማት ከሚመጡት ሰዎች ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ወደ ጤና ተቋማት ሳይመጡ በየቤታቸው የሚሞቱ እና በቫይረሱ የሚጠቁ ዜጎች መጠን ባለመታወቁ ቫይረሱ እየቀነሰ መሆኑን ማወቅ አይቻልም” ነው ያሉት ዶክተር ወንድወሰን።
አሁን ላይ ያለውን ዕለታዊ የምርመራ መጠን ከ 8 ሺህ ወደ 14 ሺህ እና ከዚያ በላይ ለማድረስ ፣ የምርመራ ውጤትን ለማወቅ እስከ 4 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን ጊዜ ወደ 30 ደቂቃ ለማሳነስ የሚያስችሉ ማሽነሪዎች ስራ ላይ በመዋል ላይ ናቸው ብለዋል።
ዜጎች ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ በቫይረሱ እንዳይጠቁ የአፍ እና አፍንጫ መከለያዎችን የመጠቀም ፣ እጅን የመታጠብ እና አካላዊ ርቀታቸውን የመጠበቅ ልምዳቸውን ሊያዳብሩ ይገባል ብለዋል።
“ቫይረሱ ለሀገር ብዙ ያበረከቱ እና የሚያበረክቱ ውድ ዜጎችን እየገደለ ነው” ያሉት ዶክተር ወንደሰን በአጠቃላይ ከ4 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ገድሏልም ብለዋል።
አሁን ላይ ያለው አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ወይም ሜካኒካል ቬንትሌተሮች ብዛት 870 ብቻ ሲሆን ፣ ተጨማሪ 530 ቬንትሌተር ያላቸው አልጋዎችን የመግዛት ሂደት መጀመሩንም ዶክተር ወንድወሰን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ 76 የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ ከ269 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ተጠቅተው 230 ሺህ 784 ሰዎች ከቫይረሱ ማገገም ችለዋል።