አረብ ኢምሬትስ እና ኢትዮጵያ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
በአረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ዴዴፎ ስምምነቶቹ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል
በአረብ ኢምሬትስ በኩል የፍትህ ሚኒስትሩ እና በኢትዮጵያ በኩል የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታው ስምምነቶቹን ፈርመዋል
አረብ ኢምሬትስ እና ኢትዮጵያ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት እና የጋራ የህግ ድጋፍን የተመለከቱ ሁለት ስምምነቶችን ተፈራረሙ።
ሁለቱ ስምምነቶች የተፈራረሙት በአረብ ኢምሬትስ የፍትህ ሚኒስትር አብዱላህ አል-ኑአይሚ እና የኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው አማካኝነት ነው፡፡
አረብ ኢምሬትስ የፍትህ ሚኒስትር አብዱላህ አል-ኑአይሚ፤ በሀገራቱ መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነትና አሁን የተደረሱት ስምምነቶችን ጨምሮ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በሁለቱም ሀገራት በኩል ያለው ፍላጎት የሚደነቅ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
የአረብ ኢምሬትስ ፍትህ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደረገውን የህግ እና የፍትህ ትብብርን ለማጠናከር፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጎልበት እና ለማዳበር እንዲሁም የትብብር ማእቀፎችን ለማስፋት ፍላጎት እንዳለውም ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ፤ የፍትህ ጽንሰ-ሃሳብን እውን ለማድረግ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እና የጋራ ስምምነቶችን አፈጻጸም በቅርበት መከታተል አስፈላጊ መሆኑም አሳስበዋል።
በአረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ዴዴፎ በበኩላቸው ፤ በሀገራቱ መካከል የተደረሱ ስምምነቶች የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አስፍረዋል፡፡
በፊርማው ስነ ስርዓት ላይ የአረብ ኢምሬትስ ፍትህ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ምክትል ጸሃፊ ኢንጂነር አብዱል ራህማን አል ሃማዲ ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ዴዴፎ እና ሌሎች የልዑኩ አባላት ተገኝተዋል፡፡