የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ህልፈን ተከትሎ የዓለም መሪዎች ወደ አቡዳቢ እያቀኑ ነው
የአውሮፓ፣አፍሪካ እና የአረብ ሀገራት መሪዎች አቡዳቢ በመግባት ላይ ናቸው
መሪዎቹ ወደ አቡዳቢ በመግባት ላይ ያሉት ሀዘናቸውን ከመግለጽ ባለፈ ከአዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ለመፍጠር ነው
የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ የዓለም መሪዎች ወደ አቡዳቢ እያቀኑ ነው።
የተባበሩት አረብ ኢምሬትን ከፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሼህ ከሊፋ ቢን ዛይድ ባሳለፍነው አርብ በ73 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ይሄንን ተከትሎም የዓለም መሪዎች ወደ አቡዳቢ በማቅናት ላይ ሲሆኑ እስካሁን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ፣የቱኒዝያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሳይድ፣ የሱዳን ወታደራዊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ጀነራል አልቡርሃን እና የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ አቡዳቢ ደርሰዋል።
በቀጣይም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን፣ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ፣ የሞሪታኒያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ኦሉድ ሼክአል ጋዝዋኒ አቡዳቢ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።
የዓለም ሀገራት መሪዎች ወደ አቡዳቢ እያቀኑ ያሉት ሀዘናቸውን ከመግለጽ ባለፈ ከአዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ለመፍጠር ነው ተብሏል።
የሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
የአቡ ዳቢው ልዑል አልጋ ወራሽ፤ ወንድማቸው ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ ባሳለፍነው አርብ ማረፋቸውን ተከትሎ ነው የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት።
የሃገሪቱ ጠቅላይ ምክር ቤት ነው ሼክ መሃመድን ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጠው። ሼክ መሃመድ ምክር ቤቱ እምነት አድሮበት ለሰጣቸው ትልቅ ኃላፊነት አመስግነዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አክለውም የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች ለሀገራቸው እና ለእሳቸው ላሳየው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።