ቻይናዊው ሚሊየነር የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ለ27ኛ ጊዜ ሊፈተኑ ነው
የ56 አመቱ ጎልማሳ ከ16 አመታቸው ጀምሮ ፈተናውን ቢወስዱም ማለፊያ ነጥብ ማምጣት አልቻሉም
የግንባታ መሳሪያዎችን የሚያቀርብ ግዙፍ ኩባንያ ያቋቋሙት ሚሊየነሩ በትምህርት መግፋት ይፈልጋሉ
በ50ዎቹ አጋማሽ የሚገኙት ቻይናዊው ሚሊየነር ሊያንግ ሺ በንግድ ስራቸው አንቱታን ያተረፉ ስኬታማ ሰው ናቸው።
በሲችዋን ግዛት የግንባታ መሳሪያዎችን የሚያቀርበው ኩባንያቸውም ትርፍ በትርፍ ላይ የሚደራርብ ነው።
ሺ አንድ ነገር ግን ሊሳካላቸው አልቻለም፤ በታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ መማር የሚያስችል ፈተናን ማለፍ።
ሚሊየነሩ ከፈረንጆቹ 1983 (በ16 አመታቸው) ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና (“ጋካኦ”) ለ26 ጊዜ ቢወስዱም ማለፊያውን ነጥብ አላገኙም።
ዘንድሮም 13 ሚሊየን ሰዎች የሚፈተኑትን ፈተና ለ27ኛ ጊዜ ለመፈተን ዝግጅት ሲያደርጉ መክረማቸውን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ሊያንግ ሺ 27ኛ ሙከራቸው በስኬት እንዲጠናቀቅ “የመነኩሴ ህይወት እየኖርኩ ነው፤ በየቀኑ ለ12 ስአታት መጽሃፍትን በማንበብ እየተዘጋጀሁ ነው” ማለታቸውም ተገልጿል።
“ዩኒቨርሲቲ ለመግባትና ምሁር ለመሆን ብጓጓም እስካሁን ሳይሳካልኝ መቅረቱ በጣም ያበሳጫል” የሚሉት የ56 አመቱ ጎልማሳ፥ ከ16 አመታቸው ጀምሮ በተከታታይ ለ10 አመት ፈተናውን ወስደዋል።
በ1992 ግን እድሜያቸው ከ25 አመት በላይ የሆኑ ፈተናውን መውሰድ አይችሉም የሚል ክልከላ ተጥሎ ፈተናውን መውሰድ አቆሙ።
ገደቡ በ2001 ሲነሳም ተስፋቸው ለምልሞ የነበረ ቢሆንም እስከ 2022 በወሰዷቸው 16 ፈተናዎች በታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ መማር የሚያስችል ውጤት አላመጡም።
ፈተናዎችን ለመስጠት ፈታኝ በነበረው የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እንኳን የ”ጋካኦ” ፈተናን በመውሰድ በትምህርት የመዝለቅ ፍላጎታቸውን ያሳዩት ሺ ዘንድሮስ በ27ኛ ሙከራቸው ይሳካላቸው ይሆን?