መንግስት፤ የህወሃት እና የኤርትራ ግጭት ወደ ኢትዮ- ኤርትራ ግጭት እንደማያመራ ገለጸ
ህወሃት ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማጋጨት ትንኮሳ እያደረገ መሆኑን መንግስት ገልጿል
ህወሓት የኤርትራ ጦር ጥቃት “እየከፈተብኝ” ነው ሲል ከሷል
በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሃት ኤርትራን እየተነኮስ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ገልጿል፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ቅዳሜ እና ዕሁድ ዕለት የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ በኩል ጥቃት ከፍቶ እንደነበር ቢገልጹም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ቀድሞ ትንኮሳ ያደረገው ህወሃት እንደሆነና በዚህም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብሏል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ህወሃት የኤርትራ ጦር ጥቃት ከፈተ በሚል የሚያሰራጨው መረጃ ትክክል አይደለም፡፡
- ህወሓት እና ኤርትራ ወደ ጠቅላላ ጦርነት ከገቡ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?
- ኤርትራ “ለብሔራዊ ደህንነቴያሰጋኛል” በሚል በድንበር አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ ቦታዎች መያዟን ጠ/ሚ ዐቢይ ገለጹ
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ቅዳሜና እሁድ ተከስቷል ካሉት ግጭት በተጨማሪ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ. ም የኤርትራ 57ኛ እና 21ኛ ክፍለ ጦሮች ወደ ትግራይ ክልል ጥቃት ሰንዝረው ነበር ብለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው የኤርትራ ጦር ጥቃት መሰንዘሩን እና አዲአዋላ በተባለው አካባቢ በነበረ ውጊያ የህወሃት ታጣቂዎች ጥቃቱ መክተዋል ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ በውጊያው በርካቶች መቁሰላቸውንና ለህልፈት መዳረጋቸውን ገልጸው የጦር መሳሪያም ጭምር መማረካቸውን ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ (ዶ/ር) ግን ትንኮሳ ያደረገው ህወሃት እንደሆነና የተመቱትም ራሳቸው የህወሃት ታጣቂዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ በኤርትራና በህወሃት መካከል ግጭት እንዲፈጠር ያደረገው ህወሃት መሆኑን ገልጸው በዚህ ሁኔታ ህወሃቶች “ሬሳ እንኳን መንሳት አልቻሉም፤ በጣም ብዙ ሰው ወድሞባቸዋል” ሲሉም ነው ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት።
አል ዐይን አማርኛ፤ በህወሃትና በኤርትራ መካከል ያለው መካረርና አልፎ አልፎ እየተደረገ ያለው ውጊያ ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደጦርነት ሊያስገባ አይችልም ወይ በሚል ለሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ወደዚያ የሚያመራ ሁኔታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ህወሃት ትንኮሰውን የሚፈፅመው ሁለቱን ሀገራት ወደ ግጭት ለማስገባት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ይህ ግን መቼም ቢሆን “አይሳከም”ብለዋል፡፡
መንግስት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ መረጃ እንዳለው ያስታወቁት ሚኒስትሩ፤ ህወሃት ኤርትራ እና ኢትዮጵያን ለማጋጨት እየሰራ ቢሆንም ሁለቱ ሀገራት መቸም ቢሆን ወደ ግጭት አይገቡም ብለዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት የኤርትራ ጦር መሳተፉን በተመለከተ በርካታ ክሶች ይቀርቡበት የነበረ ሲሆን ኤርትራ ግን ይህንን አስተባብላ ነበር፡፡
ከሰሞኑ በህወሓት ኃይሎች እና በኤርትራ መንግስት ጦር መካከል ተከስቷል ስለተባለው ግጭት የኤርትራ መንግስት እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
ከተጀመረ 2ኛ አመቱን እያገባደደ ያለው እና በትግራይ ክልል በፌደራል እና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተካሄደው ጦርነት ወደ አጎራባቸው አፋር እና አማራ ክልሎች በመስፋፋቱ ጉዳት ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሕወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩት ከአብዛኛው የአፋር እና የአማራ ክልል ቦታዎች ማስለቀቁን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ነገርግን ህወሃት ቦታዎቹን የለቀቀው ተሸንፈው ሳይሆን ለሰላም እድል ለመስጠት አስቦ እንደሆነም እንዲሁ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ሲባል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ያለ ቢመስልም አሁን ድጋሚ ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት አለ፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመሰለፍ በህወሓት ላይ ጦርነት የከፈተው የኤርትራ መንግስት ወደ ጦርነቱ የገባው በኤርትራ ላይ ተደቅኗል ያለውን የደህንነት ስጋት ለመቀልበስ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
በአሜሪካ መንግስት የሚደገፈው እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት እስካሁን ያመጣው ለውጥ የለም፡፡