ካርቱም ብሔራዊ ፍላጎቴን እስካልተጋፋ ድረስ የትኛውም ሃገር የባህር ኃይል ቤዝን ቢያቋቁም ችግር የለብኝም ብላለች
በቀይ ባህር ዳርቻ የሚገኙ ወደቦቿን ሩሲያም ሆነች ሌላ ሃገር በባህር ኃይል ቤዝነት ለመጠቀም ቢችሉ ችግር እንደሌለባት ሱዳን አስታወቀች፡፡
የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ/ል ሞሃመድ ሃምዳን ዳገሎ (ሄሜቲ) በቀይ ባህር የባህር ኃይል ቤዝን ማቋቋም ለሚፈልጉ ሃገራት በሯ ክፍት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይሄ ከብሔራዊ ደህንነቷም ሆነ ሉዓላዊነቷ የሚጋፋ እንዳልሆነ ነው ሄሜቲ የገለጹት፡፡
ሄሜቲ ከሰሞኑ በሩሲያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ እርሳቸው ሞስኮ በደረሱ በዋዜማውም ነበር የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
ከጉብኝቱ መልስ በካርቱም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማንኛውም በሱዳን የባህር ኃይልን ማቋቋም የሚፈልግ ሃገር የእኛን ፍላጎት እስካልተጋፋ ድረስ ይችላል ብለዋል፡፡
“ቀይ ባህር ላይ 730 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚረዝም የባህር ዳርቻ አለን፡፡ ሩሲያም ሆነ ሌላ በዚህ አካባቢ የጦር ቤዝን ለማቋቋም የሚፈልግ ሃገር ከፍላጎታችንና ከብሔራዊ ጥቅማችን እስካልተቃረነ ድረስ ቢያቋቁም ችግር የለብንም” ሲሉም ነው ሄሜቲ የተናገሩት፡፡ ጉዳዩ የሃገሪቱን ጦር የሚመለከት እንደሆነ በመጠቆም፡፡
ሩሲያ በሱዳን የባህር ኃይል ቤዝን የማቋቋም የረጅም ጊዜ ፍላጎት አላት፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችላትን ስምምነትም ፈጽማለች፡፡ ስምምነቱ በፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር የስልጣን ዘመን የተፈጸመ ነው፡፡ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስምምነቱን በአዋጅ ቢያጸድቁትም አል በሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡
ሆኖም የሱዳን ጦር አሁንም ስምምነቱን በመገምገም ሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ካርቱም ባሳለፍነው ጥቅምት የተፈጸመውን ወታደራዊ መፍንቅለ መንግስት ተከትሎ በከፍተኛ የገንዘብና የድጋፍ እጦት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከምዕራባውያን ይገኝ የነበረው ድጋፍም ተቋርጧል፡፡ የሄሜቲ የሞስኮው ጉብኝት ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተካሄደ እንደሆነም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
በጉብኝቱ የሩሲያ ባለሃብቶች በሱዳን ገንዘባቸውን ፈሰስ ስለሚያደርጉበት ሁኔታ ምክክር መደረጉም ተገልጿል፡፡
ሩሲያ ራሷን የመጠበቅ መብት እንዳላት የተናገሩት ደገሎ ከዩክሬን ጋር የገባችበት ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች መፈታት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ስለመወያየታቸውም ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዡ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያሉ ተቃውሞዎች ረገብ ብለው ሱዳናውያን ወደ ምርጫ ማምራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክሮችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡