ዶ/ር አሸብር ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ በእግር ኳስ ጭምር እንድትሳተፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል
በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለከፍተኛ የሜዳሊያ ቁጥር ውስጥ ከሚታጩ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ከ1956 እ.አ.አ ጀምሮ ተሳትፎዋ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪነቷም ይታወቃል።
ሀገሪቱ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በሚደረጉ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ እንዲሁም በኦሎምፒክ ሜዳዎች ሰንደቅ ዓላማዎቻቸው ከሚውለበለቡላቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ናት።
ኢትዮጵያ ባላት ረጅም የኦሎምፒክ ታሪክ አትሌቲክስ ቅድሚያውን ቢይዝም ዘንድሮ ግን ሀገሪቱ በሌሎች ስፖርቶች እንደምትወዳደር ይጠበቃል።
ከሰሞኑ በጃፓና መዲና ቶኪዮ ከተማ በሚጀመረው 32 ኛው ኦሎምፒክም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በውኃ ዋና እና በቴኳንዶ እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አስታውቀዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ወር እና አንድ ወር ተኩል ብቻ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየቱን ያነሱት ዶ/ር አሸብር፤ በዘንድሮው ዓመት ግን ላለፉት ስምንት ወራት ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር ተናግረዋል።
አትሌቶች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አትሌቶች በአዲስ አበባ ስታዲዮም ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ማሻሻላቸውንና በዓለም ላይ ደግሞ እነ ለተሰንበት ግደይ የሚያኮራ የዓለም ክብረ ወሰን ማሻሻላቸውን ገልጸዋል።
ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትና ግለሰቦችም ወደ ጃፓን ለሚጓዘው ቡድን የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንቱ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ከ57 ዓመታት ቆይታ በኋላ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዳግም ወደ ቶኪዮ የተመለሱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በወቅቱ በሻምበል አበበ ቢቂላ አሸናፊነት ሰንደቅ ዓላማዋ ተውለብልቦላት እንደነበር የሚታወስ ነው።
እ.ኤ.አ በ 1964 እነ አበበ ቢቂላ ሲወዳደሩባቸው የነበሩ ቦታዎችም ጃፓን ከ57 ዓመት በኋላ ከሰሞኑ በምታተናግደው ኦሎምፒክ ጨዋታዎች እንደሚደረጉባቸው ተገልጿል።
ዶ/ር አሸብር በዚህ ኦሊምፒክ፤ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ፣ ከብስክሌት፣ ከውኃ ዋናና ከቴኳንዶ ባለፈም በእግር ኳስም እንድትሳተፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል። ምንም እንኳን እግር ኳሱ ባይሳካም በአራቱ የውድድር አይነቶች ኢትዮጵያ ስኬታማ እንዲትሆን አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚጓዙት አትሌቶችና አሰልጣኞች 65 ሲሆኑ በጥቅሉ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ጃፓን የሚያመራው ልዑክ ከ90 በላይ አባላት እንደሚኖሩትም ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል።
አትሌቶች ውጤት አምጥተው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ እንዲል በሁሉም የውድድር አይነቶች ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል።
ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚወክለው የመጀመሪያው ልዑክ ወደ ጃፓን እንደሚያመራም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ዶ/ር አሸብር፤ በዚህ ዓመት ይህንን ያህል ወርቅ፣ ብር፣ አሊያም ነሐስ እናመጣለን የሚል ዕቅድ ላለመናገር ተቀናቃኙ ብዙ በመሆኑ ይልቁንም ወርቅ፣ ብርና ነሐስ የሚያስመጣ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ጃፓን ለሚያቀናው ልዑክ አስፈላጊ ድጋፍ አድርገዋል ሲሉም ፕሬዝዳንት አሸብር ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት የሚደረገው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች አገራዊና ሕዝባዊ አንድነትን ለማምጣት እንደሚያግዝም የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በቶኪዮ በ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በአትሌቲክሰ፣ በውሃ ዋና፣ በቴኳንዶና በብስክሌት የስፖርት አይነቶች ለሚወክሉ አትሌቶች አሸኛኘት አድርገዋል።
ርዕሰ ብሔሯ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከቡድኑ ለተወከሉት አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ አስረክበዋል።
ዶ/ር አሸብርና ኮሎኔል ደራርቱ መካከል አለመግባባት አለ?
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መካከል አለመግባባቶች እንዳሉ በተለያዩ መንገዶች ሲገለጹ ነበር፤ ይህንን በተመለከተ አል ዐይን የጠየቃቸው ዶ/ር አሸብር “ እኛ ምንም ችግር የለብንም፤ አብረን ነው የምንሰራው፤ ስፖርቱ ላይ ብዙ ጊዜ ያለመግባባቶች ያጋጥማሉ፤ በመሰረቱ ያለመግባባትም ኖሮንም አያውቅም“ ሲሉ ተናግረዋል።
አለመግባባት እንዳለ ሲወራ እንደሚሰሙ ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በቅርቡ ተገናኝተው ምን ምን መስራት እንደሚገባቸው የስራ ክፍፍል እንዳደረጉ አንስተዋል።
ዶ/ር አሸብር፤ አሁንም ቢሆን ስራዎችን እየሰሩ ያሉት በመመካከር እንደሆነ ገልጸው እንደዚህ አይነት ጭምጭምታዎች ብዙ እንደማይጠቅሙና ምንም ችግር እንደሌለ አንስተዋል።
ኮሚቴው እና ፌዴሬሽኑ አብረው እየሰሩ መሆኑን፤ ፌዴሬሽኑም የራሱን፤ ኮሚቴውም የሚጠበቅበትን ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ “የእኛን ጎደሎ እነሱ እየሞሉ የነሱን እየሞላን ነው እየሄድን ያለነው፤ ወደፊትም በዚህ አይነት ነው መሆን ያለበት” ብለዋል።
ከኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በስራ ጉዳይ እንደሚያወሩና እርሷም ብትሆን ኃይል ቃል መናገር የማትፈልግ መሆኗም ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል።
በአዲስ መልክ የተዘጋጀው የቶኪዮ ብሔራዊ ስታዲየም የመክፈቻና መዝጊያ መርሃ ግብር እንደሚያስተናግድ የተገለጸ ሲሆን የአትሌቲክስ ውድድርም (ሩውዝ (ሩጫ፣ ውርወራ፣ ዝላይ) ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።