በየመን የሚገኙ 1 ሺ 200 ኢትዮጵያውያንን ለመመለስም የሰነድ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ኢትዮጵያ በቅርቡ 180 ዜጎቿን ከቤሩት ትመልሳለች
በሊባኖስ የሚገኙ 180 ኢትዮጵያውንን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዜጎቹን ለመመለስ የሚያስችሉ የሰነድ ማዘጋጀት ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው ያሉት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሰሞኑ ወደሃገራቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ከአውሮፓ ህብረት እና ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም እንዲሁም ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ያሉም ሲሆን 1 ሺ 200 ዜጎችን ለመመለስ ሰነድ የማዘጋጀት ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተግባሩ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው ሌሎች ሃገራት እንደሚቀጥልም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
የሚኒስቴሩን ሳምንታዊ ተግባራት በተመለከተ አምባሳደር ዲና ዛሬ ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ በተለያዩ የውጭ ሃገራት ኢትዮጵያን ከወከሉ አምባሳደሮች እና ሚሲዮኖች ጋር ተወያይተዋል ያሉ ሲሆን ሚሲዮኖቹ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተቀራርበው መስራት በሚችሉባቸው መንገዶች ዙሪያ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል፡፡
አዲስ የተሾሙ የሱዳን፣ የጀርመን፣ የግሪክ እና ሞውሪታኒያ አምባሳደሮች በዚህ ሳምንት የሹመት ደብዳቤ ቅጂያቸውን አቅርበዋልም ነው ያሉት፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ በዚሁ ሳምንት በጅቡቲ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመብት አያያዝ ውይይት ተደርጓል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉም በተያዘው ወር መባቻ ወደ ጅቡቲ አቅንተው ከሃገሪቱ መንግስት የመከላከያ፣የፖሊስና የደህንነት ባለስልጣናት እንዲሁም ከኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከዓለም የስደተኞች ድርጅት ተወካይ እና ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጋር ተገናኝተው በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ባሉበት ሆነው ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች እና የጅቡቲ መንግስት የዜጎችን መብት እንዲጠብቅ ስለመምከራቸውም ነው የገለጹት፡፡
አምባሳደር ዲና ከሚቀጠለው ሰኞ ነሀሴ 18 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚዘልቅ ዓመታዊ የአምባሳደሮች እና የሚሲዮን መሪዎች ስብሰባ በቢሾፍቱ ከተማ ይካሄዳል ብለዋል።
ስብሰባው “ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳችን ለዘላቂ ሰላም፤ለጋራ ተጠቃሚነትና ለአገራዊ ብልጽግናችን’’ በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ነው፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የሚሲዮኖቹ አፈጻጸም ይገመገማል በቀጣይ 5 እና 10 ዓመታት መሪ እቅድ ላይም ውይይት ይደረጋል፡፡
የተሻሻለው ነገር ግን ገና ያልጸደቀውን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂን ጨምሮ በተለያዩ አገራዊ ፖሊሲዎች ስልጠና ይሰጣልም ያሉት ቃል አቀባዩ ጉብኝቶች እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡