እስራኤል በዚህ ዓመት መጨረሻ 4,500 ፈላሻዎችን ከኢትዮጵያ እወስዳለሁ አለች
ወደ እስራኤል ለመጓዝ አስፈላጊ ሂደቶችን ያጠናቀቁ 8,000 ያህል ፈላሻዎች በአዲስ አበባ እና በጎንደር ይገኛሉ
በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀሪ ፈላሻዎችን በ3 ዓመታት ጊዜ ዉስጥ ወስዶ ለመጨረስ መታቀዱ ተገልጿል
እስራኤል በዚህ ዓመት መጨረሻ 4,500 ፈላሻዎችን ከኢትዮጵያ እወስዳለሁ አለች
የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የስደተኞች ሚኒስትር ፕኒና ታማኖ-ሻታ ዛሬ ይፋ ባደረጉት ዕቅዳቸው በዚህ ዓመት መጨረሻ 4,500 ፈላሻዎችን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመውስድ ዝግጅት እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2023 ወደ እስራኤል እንደሚገቡ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
ታማኖ-ሻታ ዕቅዳቸውን በሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ለስደተኞች እና ዳያስፖራዎች ጉዳይ ኮሚቴ በዝርዝር ባቀረቡበት ወቅት ፣ በዓመቱ መጨረሻ ወደ እስራኤል ከሚገቡት ፈላሻዎች (ቤተ እስራኤላውያን) አብዛኛው ወደ እስራኤል ለመግባት አመልክተው ከ10 ዓመታት በላይ የጠበቁ ናቸው፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ዴቪድ ቢታን እቅዱን በአብዛኛው ያጸደቁ ሲሆን ወደ እስራኤል ለመግባት ብቁ የሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፈላሻዎች ሙሉ በሙሉ በ2023 ተጠቃልለው እንዲገቡ የተያዘው ዕቅድ ሩቅ መሆኑን በመጥቀስ በ2021 እንዲጠናቀቅ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ፈላሻዎች በጎንደር የአምልኮ ስፍራ እኤአ 2016-ሮይተርስ
በጊዜ ተጠቃልለው እንዲገቡ የተፈለገበት ምክንያት ደግሞ ወደ አስራኤል ለመጓዝ አስፈላጊ ሂደቶችን ጨርሰው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እና በጎንደር መጠለያዎች ተለይተው የሚገኙ 8,000 ያህል ፈላሻዎችን በመውሰድ መጠለያዎቹን ለመዝጋት በማሰብ ነው፡፡ በአዲስ አበባ እና በጎንደር መጠለያዎች ይገኛሉ ከተባሉትኙ 8,000 ገደማ ፈላሻዎች መካከል በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ እስራኤል ይገባሉ የተባሉት ከ 4,500 በላይ የሚሆኑት በእስራኤል የቤተሰብ አባላት የሆኑ ዘመዶች ያሏቸው እንደሆኑ ኢየሩሳሌም ፖስት ዘግቧል፡፡ እነዚህን ወደ እስራኤል ለመውሰድ ኮሚቴ መቋቋሙን ሚኒስትሯ ታማኖ-ሻታ ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የሚሄዱ ፈላሻዎች ‘ወደ እስራኤል መመለስ’ በሚለው ህግ ሳይሆን ‘ከቤተሰብ ጋር ዳግም መገናኘት’ በሚለው ህግ መሰረት እንደሚወሰዱ ነው የተገጸው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፈላሻዎች በአይሁድ ህግ መሰረት የአይሁድ ዘሮች እንጂ አይሁዳውያን ስላልሆኑ ነው፡፡ አያቶቻቸው በጊዜ ሂደት ኃይማኖታቸውን ወደ ክርስትና በመቀየራቸው ምክንያት ‘ወደ እስራኤል መመለስ’ የሚለውን ህግ እንደማያሟሉም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡