ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያቸው 92 ሃገራት ክትባቱን በቀጣዩ ዓመት ያገኛሉ ተብሏል
ኢትዮጵያ የቫይረሱን ክትባት በርካሽ እንደሚያገኙ ከሚታሰቡ ሃገራት መካከል አንዷ ናት
ኢትዮጵያ የኮሮና ክትባቶችን በርካሽ ከሚያገኙ 92 ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ጋቪ ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ደረጃቸውን የጠበቁ አንድ መቶ ሚሊዬን የቫይረሱን ክትባቶች በፍጥነት ለማምረት የሚያስለውን ሰምምነት ሴረም ከተሰኘው የህንድ የክትባቶች አምራች ተቋም ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡
ሴረም አስትራ ዜናካ እና ኖቫቫክስ በተባሉ የምርምር ተቋማት በመዘጋጀት ላይ ያሉ ክትባቶችን ነው የሚያመርተው፡፡
ክትባቶቹ ዓለም ጤና ድርጅትን ይሁኝታ አግኝተው ወደ ምርት እንደሚገቡ የሚፈቀድ ከሆነ ሴረም በስፋት አምርቷቸው እስከ ቀጣዩ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አጋማሽ ደረስ ለተጠቀሱት ሃገራት ይደርሳሉ ተብሏል፡፡
አዳዲስ ምርመራዎች፣ክትባቶች እና መድሃኒቶች በተገኙ ቁጥር ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሃገራት የተገኙትን ለማግኘት ሲቸገሩ አይተናል ያሉት የጋቪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሴት በርክሌይ ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ ነገሮች እንዲቀየሩ እንፈልጋለን ብለዋል ክትባቶቹን በማግኘት ረገድ በደሃና ሃብታም ሃገራት መካከል ልዩነቶች ሊኖሩ እንደማይገባ ለመግለጽ፡፡
የጋቪ ቦርድ እውቅና የሰጣቸው 92ቱ ሃገራትም ኮቫክስ በተሰኘው የትብብሩ አዲስ የፋይናንስ ስርዓት በመታገዝ ክትባቶቹን ከሶስት ዶላር (መቶ አስር ብር ገደማ) ባልበለጠ ዋጋ የሚያገኙ ይሆናል፡፡
የስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተመረጡ 92 ሃገራት ዝርዝርም ባሳለፍነው ሳምንት በጋቢ ቦርድ ጸድቋል፡፡
ከነዚህ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ በኢትዮጵያ 35 ሺ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የሚታወቅ ነው፡፡