አየር ኃይሉ 17 የአል-ሻባብ የፈንጅ ቡድን አባላትን ደመሰሰ
በሶማልያ ልዩ ስሙ ኮርቶሌ እና ህርኩት በተባሉ አካባቢዎች በተወሰደ ጥቃት መደምሰሳቸው ተነግሯል
አባላቱ ከዶሎ ወደ ባይደዋ ወታደራዊ ቁሣቁሶችን ጭኖ በተንቀሣቀሠ የወገን ኮንቮይ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አስበው ነበር ተብሏል
የኢፌዲሪ አየር ኃይል 17 የአል-ሻባብ የፈንጅ ቡድን አባላትን መደምሰሱን አስታወቀ
በሶማልያ ልዩ ስሙ ኮርቶሌ እና ህርኩት በተባሉ አካባቢዎች በተወሰደ ጥቃት 17 የአልሸባብ የፈንጅ ቡድኑ አባላት ሙሉ በሙሉ መደምሰሣቸውን በኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ምድብ አስታውቋል፡፡
የፈንጅ ቡድኑ የተደመሠሠው "መነሻውን ዶሎ በማድረግ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሶማልያ ባይደዋ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሣቁሶችን ጭኖ በተንቀሣቀሠ የወገን ኮንቮይ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጉዞውን ለማዎክና ለመግታት አስቦ" የነበረ በመሆኑ ነው እንደ አየር ምድቡ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮ/ል ሀብቶም ዘነበ እና የተዋጊ ሄሊኮፕተር ክንፍ አዣዥ ሻለቃ ደረሥ እንዳለ ገለጻ።
ቡድኑ በርካታ ፈንጆችን በመቅበር በወገን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አቅዶና አደራጅቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ የገለፁት ሃላፊዎቹ "የአልሸባብ እቅድ ሳይሳካ የቡድኑ አባላትን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ የወገን ጦር ያለስጋት እንዲንቀሳቀስ በማስቻል ድጋፍ ሰጭነታችንን በተግባር አሣይተናል" ብለዋል፡፡
አየር ምድቡ "ህዝብና መንግስት የሰጠውን ህገ መንግስታዊ አደራ በታማኝነትና በብቃት በመወጣት ዛሬም እንደትናንቱ የቀጠናውን አየር ክልል ነቅቶ በመጠበቅ በአገር ላይ የሚቃጣ ማኝኛውም ትንኮሳ የመመከት አቅምና ብቃት" እንዳለውም ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮ/ል ሀብቶም ዘነበ ስለማስታወቃቸውም ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።