አዋጁ የኮሮና ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት መታወጁ ተገልጿል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ
የኮሮና ወረርሽኝ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
መላውን ዓለምን እየፈተነ የሚገኘውን ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ደረጃ በደረጃ የመፍትሔ ርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመከላከል ስትራቴጂ ላይ ያተኮሩ ግንዛቤን የመፍጠር፣የሕክምናና የማቆያ ሥፍራዎችን የማዘጋጀት፣የመከላከያና የሕክምና መሣሪያዎችን ከውጭ የማስገባት እና ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በቫይረሱ የተያዙ ወገኖች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን አሁን ያሉን መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት እየተባባሰ ከመጣው ወረርሽኝ ሕዝብና ሀገርን ለማዳን ሲባል መንግስት አስቸጋሪ እና የወደፊቱንም ትውልድ የሚመለከት ነው ያሉትን ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቀምጠዋል፡፡
”ይሄንን አስቸጋሪ ጊዜ ልናልፈው የምንችለው በአካል ተራርቀን በመንፈስ ግን አንድ ሆነን ከቆምን ብቻ ነው፡፡ የያንዳንዳችን ሀብት የሁላችን፣ የእያንዳንዳችንም ችግር የሁላችን መሆን አለበት“ም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሀገርን ለማዳንና ትውልድን ለመታደግ ከዚህ በላይ ልንወስን እንደምችልም መታወቅ አለበት”፡ ሲሉም ነው “ዜጎቻችንም ከዚህ በላይ ግዴታቸውን ለመወጣት ወገባቸውን አጥብቀው መጠበቅ አለባቸው” በሚል ባሰፈሩት ጽሁፍ ያስታወቁት፡፡
ችግሩን ለመቋቋም ከሚሠሩት አካላት ጋር ሁሉም አብሮ እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡም ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ ችግሩን ለማባባስ የሚሠሩ ካሉ ግን፣ በሕጉ መሠረት የማያዳግም ርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከአሁን ቀደም ሲያደርጉ እንደነበረው ሁሉ ሊረዳዱና ሊደጋገፉ አቅመ ደካሞችን ሊረዱ እንዲሁም የቤት ተከራዮቻቸውን ዕዳ ሊካፈሉ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የመከላከያ ና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት ባለሞያዎች፣ የሚዲያ እና በመገናኛ መሥመሮች ላይ 24 ሰዓት የሚያገለግሉ ዜጎች ተገቢው ምስጋናና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ብለዋል፡፡
አርሷደሩ ራሱንና ቤተሰቡን ከወረርሽኙ እየጠበቀ የበልግ ወራት የምርት ተግባራቱን እንዲያከናውንም አደራ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንዱስትሪዎች ለሰራተኞቻቸው ህይወት እየተጠነቀቁ ማምረታቸውን መቀጠልና በምርት ዝውውር ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ያሉም ሲሆን ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን ለመተካት ለሚደረገው ጥረት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የሚሰጡ መመሪያዎችን ማክበርና መተግበር እንዲሁም መተባበር እንደሚያስፈልግም ዶ/ር ዐቢይ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
የአዋጁን ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ነገር የለም፡፡