የትራንስፖርት ሚንስቴር በበኩሉ ልዩ ባሶች መጀመሪያ አሰራራቸውን ከደላላ የጸዳ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የልዩ ባስ ትራንስፖርት አገልግሎት እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ዘርፉም በተጠቃሚዎች ብዛት እና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሲጨምር ቆይቷል።
ከኢትዮጵያ ልዩ ባስ ትራንስፖርት ማህበራትና ድርጅቶች ህብረት እንደገለጸው ከዚህ በፊት በየዓመቱ ወደ ገበያው የሚገቡ ድርጅቶች እና ከአውቶቡሶች ብዛት እየጨመረ የመጣ ነበር።
ይሁንና ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከገበያ የሚወጡ አውቶቡሶች እና ድርጅቶች መኖራቸው ተገልጿል።
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሙሉቀን መለሰ ለአል ዐይን እንዳሉት ከዚህ በፊት ቢያንስ ሶስት ድርጅቶች በዓመት የልዩ ባስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍን ይቀላቀሉ ነበር ብለዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመት ውስጥ ግን በመለዋወጫ እጥረት፣ በጸጥታ እና ደህንነት ችግሮች ምክንያት የልዩ ባስ ትራንስፖርት ዘርፍ እየተፈተነ ነው ብለዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለብዙ ጊዜያት የልዩ ባስ ትራንስፖርት ዘርፍን ፈትኗል ያሉት ሊቀመንበሩ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ትራንስፖርት ዳግም መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ይሁንና በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ያለው የጸጥታ ችግር ባለመፈታቱ የልዩ ባሶች ወደነዚህ አካባቢዎች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ልዩ ባሶች በመለዋወጫ እትረት ምክንያት አገልግሎት እንዳይሰጡ እና ከገበያ እያስወጣቸው መሆኑንም አቶ ሙሉቀን አክለዋል።
እቅዳችን የሀገር ውስጥ ትራንስፖርት ፍላጎትን በማሟላት ከአዲስ አበባ አስመራ፣ ናይሮቢ እና ጅቡቲ መጀመር መሆኑንም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።
መንግሥት የልዩ ባስ ትራንስፖርት አገልግሎት የገጠማቸውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እና የጸጥታ ችግሮችን እንዲፈታም አቶ ሙሉቀን መለሰ ጠይቀዋል።
በትራንስፖርት ሚንስቴር የልዩ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ አሽከርካሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ከድልማግስት ኢብራሂም በበኩላቸው የልዩ ባስት ትራንስፖርት ጥራትን ለማሻሻል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ውንደ አቶ ከድልማግስት ገለጻ "የልዩ ባስ ትራንስፖርት የአውሮፕላን ቲኬት መግዛት ላልቻሉ ነገር ግን ከመደበኛ አውቶቡስ ከፍ ያለ አቅም ላላቸው ደንበኞች የተዘጋጀ የትራንስፖርት አማራጭ ነው።"
የልዩ ባስ ትራንስፖርት ለሌሎች የየብስ ትራንስፖርት አማራጮች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ አርዓያ የሚሆን ስራ እንዲሰሩ ቢጠበቅባቸውም ያንን እያደረጉ አይደለም ሲሉም አቶ ከድልማግስት ተናግረዋል።
"የልዩ ባስ ትራንስፖርት የጉዜ ትኬት በደላላዎች የሚቸበቸብ እና ግልጽ አሰራርን የማይከተሉ ናቸው" የሚሉት አቶ ከድል ማግስት "ድርጅቶቹ የኤሌክትሮኒክስ ቲኬት ለደንበኞች እንዲሸጡ ቢጠበቅባቸውም ይህንን እያደረጉ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።
- በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊደረግላቸው ነው
- በፀጥታ ስጋት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ትራንስፖርት ሚንስቴር የልዩ ባስ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን አዲስ መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል ።
"አዲሱ መመሪያ ተዘጋጅቶ ተጠናቋል" የሚሉት አቶ ከድልማግስት ከነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ. ም ጀምሮ መመሪያው እንዲተገበር የመጨረሻ ሂደር ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
"አዲሱ የልዩ ባስ ትራንስፖርት አገልግሎት መመሪያ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረግ ዋነኛ አላማው ነው" የሚሉት አቶ ከድልማግስት በተለይም ኢ-ቲኬት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶቡስ ጥራት እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማሻሻል ያስችላልም ብለዋል።
የልዩ ባስ ትራንስፖርት ማህበራትና ድርጅቶች ህብረት ያቀረባቸው የውጭ ምንዛሬ እና የጸጥታ ችግሮችን ሚንስቴሩ እንዴት ሊፈታ አስቧል? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም " የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ እንደ ሀገር ያጋጠመ ችግር ቢሆንም በተቻለ መጠን ትኩረት እንዲሰጠው እናደርጋለን፣ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ግን ከፌደራል፣ የክልል፣ የወረዳ እና የከተማ ከንቲባዎች ጋር በጋራ እየሰራን ነው ቀስ በቀስ እየተፈታ ይሄዳል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ300 በላይ ልዩ አውቶቡሶች መካከለኛ ለሚባለው ማህበረሰብ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ከትራንስፖርት ሚንስቴር ያገኘነው ማስረጃ ያስረዳል።