መካና መዲና ቁልፍ የሚይዙት መሰረታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ “አግዋቶች” ናቸው- ፕ/ር አደም ካሚል
ኢትዮጵያን በነብዩ መሐመድ ለስደት የተመረጠችው ሰላምና ፍትህን ለማግኘት ነው
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኢትዮጵያን “የእውነት ምድር” ብለው ሰይመዋታል
መካና መዲና ቁልፍን የሚይዙት መሰረታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ “አግዋቶች” መሆናቸውን ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ መሰረታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ “አግዋቶች” በመካ እና በመዲና 42 የስራ አይነቶች እንደነበራቸው ይናገራሉ።
“አግዋቶቹ መካ እና በመዲና ውስጥ የሀገር መሪ ሲመጣ ተቀብለው ያስተናግዳሉ” ያሉ ሲሆን፤ “ስፍራውን በማጽዳት እንዲሁም ቁልፍ መያዝ፣ የመክፈትና መዝጋት ስራዎችን ይሰሩ ነበረ፤ በዚህም በጣም ትልቅ ከበሬታ ነበራቸው” ብለዋል።
“በአግዋቶች ህግ እና ደንብ ላይ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ ይከለከል ነበር” ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ ንጉስ አብዱልአዚዝ ሳዑዲን ሱያቋቁሙ በዚህ ላይ ራሳቸው መስክረው ፈርመውበት እንደነበረ አስታወሰዋል።
የንጉስ አብዱልአዚዝ ልጅ ንጉስ ሳዑዲ እንዲሁም በንጉስ ፋይሰል ዘመንም የአግዋቶች ህግ እና ደንብ ተግባራዊ ነበር ያሉ ሲሆን፤ ሆኖም ግን በንጉስ ፋህድ ዘመን በመጀመሪያው ዙር ተግባራዊ ከሆነ በኋላ እየቆየ በግማሽ መጣስ መጀመሩንም ይናገራሉ።
ንጉስ ፋህድ ወደ መጨረሻው ዘመን “የተቀደሰው መካና መዲና አገልጋይ” የሚለው የአግዋቶችን ማዕረግ በማንሳት የራሳቸው ማእረግ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል።
በመቀጠልም ስራቸውን መቀማት መጀመሩን ያነሱት ፕሮፌሰር አደም፤ በዚህም እዛ ያሉ አግዋቶች በአዲስ እንዳይተኩ አዋጅ ማውጣታቸውን እንዲሁም እዛ ያለው የአግዋቶች ስራ በኩባንያ እንዲተዳደር የማድረግ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ማንኛውም መሪ ወደ መካ እና መዲና ሲመጣ ለበረከት ሲባል ለአግዋቶች ቤት እየገዛ ይሰጥ እንደነበረም በማስታወስ፤ በኋላ ላይ በስጦታ መልክ የተሰጣቸውን ቤቶች ከአግዋቶቹ ቀምተው የራሳቸው መዝናኛ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ መሰረታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ “አግዋቶች” በመዲና ላይ ቁጥራቸው ተመናምኖ ወደ አምስት ብቻ ናቸው የቀሩት ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ “ቁልፏም አሁን ላይ ኑረዲን በሚባሉ አግዋት እጅ ነች ያለችው” ብለዋል።
መካ ላይም አራት አግዋቶች ብቻ መቅረታቸውን እና እነሱም ማርጀታቸውን በማንሳት፤ እነዚህ ሲሞቱ ሌላ እንዳይተካ በአዋጅ በመከልከሉ እዛ የነበረን ታሪክ እዛ ያበቃል ብለዋል።
“አግዋቶች” መካና መዲና ውስጥ የሚገኙ የነቢዩ መስጊድ ተንከባካቢዎች፣ ካፍ ችና ዘጊዎችእንዲሁም ጠባቂዎች እንደሆኑ ይነገራል።
ፕሮፌሰር አደም ካሚል አክለውም ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኢትዮጵያን የመረጡት ሰላምና ፍትህን ለማግኘት ብለው እንደሆነም ተናግረዋል።
“ነብዩ መሐመድ ዕድሜያቸው 40 ዓመት እስከሚሞላ ድረስ ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸው በማስታወስ፤ ከዛ በኋላ የነበረው ጊዜ አስከፊ ነበር” ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ “አላህ በጠቆማቸው መሰረት ሀበሻን (ኢትዮጵያን) መረጡ” ብለዋል።
በወቅቱ ለተከታዮቻቸው “እናንተ ተከታዮቼ ሆይ ጥሪዬን በመቀበላችሁ ለችግር የተጋለጣችሁ ስለሆነ እፎይታ እስክታገኙ ወደ አንድ ቦታ ሄዳችሁ ብትጠለሉ፤ ፍትህና ሀቅን ሀበሻ ሄዳችሁ ታገኛላችሁ” ብለው እንደነበረም ተናግረዋል።
ነብዩ መሃመድ ኃይል አግኝተው መካን እስከሚያስከፍቱ ድረስ በሀበሻ የነበሩት ሙስሊሞች ለእስልምና መጠባበቂያ እንደነበሩም ገልፀዋል።
ነብዩ መሃመድ ሀበሻን “የእውነት ምድር” ብለው ሰይመዋታል ያሉ ሲሆን፤ “ፍትሃዊ ንጉስ እና ፍትሃዊ ህዝብ ያለባት ምድር ናት” ማለታቸውንም አስታውሰዋል።
ለዚህም “ሀበሻ (ኢትዮጵያ) 23 የቁርአን አንቀጾች ኢትዮጵያን ያመሰግናል” ያሉ ሲሆን፤ “ነብዩ መሃመድ ብቸኛ ቆመው ያነስተናገዱት ዜጋ የሀበሻ ዜጋ ብቻ ነው” ብለዋል።
ከዛ በኋላ በነበሩ ግጭቶችም በርካታ ሙስሊሞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ተጠልለው እንደነበረም ነው ፕሮፌሰር አደም ያስታሰዉት።
ከዚህ በመነሳትም “ኢትዮጵያውያን በአረቡ ዓለም ስንሄድ ከፍተኛ ክብር እና ተቀባይነት አለን” ያነሱት ፕሮፌሰር አደም፤ “አኔ ወደ ውጭ ሀገራት ስሄድ በተለይም በሙስሊሙ ዓለም ስጓዝ በርካታ ክብር አገኛለሁ” ብለዋል።
ለአብነትም “ወደ ቱርክ ለማስተማር ስሄድ ማስተማሪያ አዳራሹ ይሞላል፤ ጨርሼ ስወጣ የነጃሺ ዜጎች፣ የቢላል ዜጎች እያሉ ለበረከት ከፀጉሬ ቆርጠው የወስዳሉ” ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ “ወደ ፓኪስታን ስሄድም ቤታችን ገብተህ ውጣልን ብለው ይሸከሙኛል” ብለዋል።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ይህንን በአረቡ ዓለም ሀገራት ያለውን ተቀባይነት በአግባቡ አለመጠቀሟን አስታውሰው፤ በዚህ ላይ ቢሰራበት ሀገሪቱ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች ብለዋል።