የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት፡ መንግስት “ታሪካዊ ቦታዎቻችንንና ቅርሶቻችንን” ይጠብቅ
አልነጃሺ መስጅድ በትግራይ ክልል ውቅሮ አካባቢ የሚገኝ ቀደምት መስጅድ ነው
ም/ቤቱ የደረሰውን ጉዳት መጠን የሚያጣራ ቡድን ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ወደ ቦታው ማምራቱን ገለጸ
በቅርቡ በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰበትን አልነጃሽ መስጊድን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት መንግስት ታሪካዊ ለሆኑ የእስልምና ቅርሶችና ቦቻዎች “ልዩ ጥበቃ” እንዲያደርግላቸው ጠይቋል፡፡
አልነጃሺ መስጅድ በትግራይ ክልል ውቅሮ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ታሪካዊ መስጅድ ነው፡፡
ምክርቤቱ በመግለጫው”…የአለም ቅርስ በሆነው የመስጅድ እና የቀብር ቦታ በከባድ የጦር መሳሪያ“ መጠቃቱንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱና መገልገያ ቁሳቁሶች መዘረፋቸውን አስታውቋል፡፡
ንጉስ ነጃሺ የተቸገሩ ሰደተኞችን መቀበላቸውን የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አርአያ አድርገው ነበር ያለው መግለጫው፣ በመስጅዱ ላይ የደረሰው ጉዳት ያሚያሳዝን እንዲሁም የኢትዮጵያውያንንና የዓለም ሙስሊኖችን ልብ የሰበረ ነው ብሏል፡፡
መግለጫው በቅርሱ ላይ የደረሰውን ትክክለኛ ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በትብብር ወደ ቦታው መላኩን አስታውቋል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአልነጃሺ ላይ ጥቃት መድረሱን አረጋግጠው፣ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግ ገልጸው ነበር፡፡
በመስጅዱ ላይ ጉዳት የደረሰው በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን ሲመራ በነበረው ህወሃት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ጦርነት ካመራ በኋላ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት የክልሉን ዋና ከተማ ተቆጣጥሮ ወንጅለኞችን እየፈለገና የህግ ማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል፡፡