ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በ1 ዶላር ከ35 ብር በላይ ጭማሪ ታይቷል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ አዲስ የምንዛሬ ዋጋ በማውጣት ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ሃምሌ 27 2016 የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋን 95.69 ብር አድርሶታል።
የእንግዝሊ ፓውንድ በ116.68 ብር እየገዛ በ123.68 ብር እንደሚሸጥም አስታውቋል።
ገዳ ባንክ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ከ100 ብር በላይ በማድረስ የመጀመሪያው ሆኗል። ባንኩ ባወጣው እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን አንድ ዶላር በ102.01 ብር ገዝቶ በ107.11 ብር እየሸጠ መሆኑን አመላክቷል።
ዳሽን ባንክ በበኩሉ የዶላር መግዣ ዋጋ ትናንት በነበረበት እንዲቀጥል ያደረገ ሲሆን በመሸጫው ላይ ግን የ2 ብር ጭማሪ አድርጓል።
ኦሮሚያ ባንክ ባወጣው እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን አንድ ዶላርን በ90.60 ብር እየገዛ በ102.38 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
አዋሽ ባንክ በበኩሉ አንድ ዶላር በ96.30 ብር እየገዛ በ106.89 ብር እየሸጠ ይገኛል።