የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሱዳን ጦር ላይ ጥቃት ሰነዘረ እየተባለ የሚነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው ሲል መንግስት አስታወቀ
ሱዳን የኢትዮጵያ ሀይሎች በከፈቱብኝ ጥቃት በርካታ ወታደሮቼ ሞተውብኛል ብላለች
በሱዳን ድንበር በኩል የገባ የህወሓት ኃይልን የመከላከያ ሰራዊት እና የአካባቢው ሚሊሻ እንደመታቸው መንግስት ገልጿል
የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በሱዳን ጦር ላይ ጥቃት ሰነዘረ እየተባለ የሚነዛው ወሬ መሰረት ቢስ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሰት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ሱዳን ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሀይሎች ጥቃት ሰንዝረውብኛል በሚል በምታቀርበው ቅረየታ ላይ ለኢቲቪ ምላሽ ስጥተዋል።
ዶ/ር ለገሰ በምላሻቸውም፣ ህወሓት በተለያየ መልኩ ሱዳን ውስጥ የሚያሰለጥናቸውን ሰርጎ ገቦች በተለያየ ቦታ በተለይም በመተማ አካባቢዎች በተለያየ ጊዜያት ያስገባል ፤ በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚተናኮሉ ሰርጎ ገቦች ይገባሉ ብለዋል።
በዚህ መሰረት "በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰርጎ ገቦች፣ ሽፍታዎች እና አሸባሪዎች በዛ መስመር ገብተው ነበር በዛ መስመር የገባውን ኃይል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአካባቢው ሚሊሻ መቷቸዋል፤ ደምስሷቸዋል" ብለዋል።
የተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚነዙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሱዳን ጦር ላይ ጥቃት ፈፅሟል የሚለው መሰረተቢስ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የትኛውም ሉአላዊ ሀገር ላይ ጥቃት የመፈፀም አጀንዳ የለውም ሲሉም አስረድተዋል።
"መከላከያ ሰራዊቱ ጥቃት የመሰንዘር አጀንዳ ቢኖረው ኖሮ የሱዳን ኃይሎች ወረው በግድ የያዙት መሬት አለ ፤ ይሄንንም በሰላማዊ ሁኔታ በውይይት እና በድርድር እንፈተለን ብሎ የተቀመጠ ነው የኢትዮጵያ መንግስት ፤ አዲስ የመጣ የተከሰተ ነገር የለም " ሲሉ ተናግረዋል።
"ነገር ግን የህወሓትን ተልዕኮ ለማስፈፀም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ሽፍታዎችን ደምስሰናቸዋል" ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አልፋሽቃ በሚባለው አካባቢ ላይ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች እና ሚሊሻዎች በሰነዘሩት ጥቃት በርካታ ወታደሮች እንደሞቱባት አስታወቃ ነበር።
ሮይተርስ ከስፍራው አገኘው ባለው መረጃ በጥቃቱ 6 የሱዳን ወታደሮች እንደተገደሉ አስታወቋል።