“ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ኢትዮጵያን አሁንም ከገጠማት መከራ ለመታደግ “የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ጠላቶቻችን በውጭና በውስጥ ተቀናጅተው ዘምተውብናል”ም ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው ጥቁር ሕዝቦች “ለጥቁሮች ክብርና ልዕልና ሲሉ በፓን አፍሪካ መንፈስ” ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከነገ ጀምሮ ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ አስታወቁ።
“ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን! ሲሉ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን የተመለከተ መግለጫ ያወጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመስዋዕትነት ነፃነቷን አስጠብቃ መኖሯን በመግለጫቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ክብር “በችሮታ የተገኘ” እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
“ጥቅምት 24 የተጨፈጨፈው ሰራዊቱ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብም ጭምር ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት “ዐቅም የፈቀደውን ሁሉ” መደረጉንም ነው የገለጹት።
“ፖለቲካችን ከመገዳደል ወደ መተጋገል እንዲቀየር ታግለናል”ም ብለዋል፤ “በሰው ሀገር የሚንከራተቱት ሁሉ እንዲገቡ”ለማድረግ መሞከሩንና “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር”በሚል አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን በመጠቆም።
ጠ/ሚ ዐቢይ በወሎ ግንባር በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች መሳተፋቸውን ገለጹ
“ኢኮኖሚው እንዲያገግምና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፤ የዳኝነት ሥርዓታችን እንዲሻሻል፣ የሰብአዊ መብት አያያዛችን እንዲስተካከል፤ የውጭ ግንኙነት መርሐችን ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ታግለናል”ም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
መከራን የማለፍ “ነባር” ችሎታ አላት ያሉላትን ኢትዮጵያን አሁንም ከገጠማት መከራ ለመታደግ “የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ጠላቶቻችን በውጭና በውስጥ ተቀናጅተው ዘምተውብናል”ም ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ።
ትግሉ የመላ ጥቁር ሕዝቦች እንደሆነና ኢትዮጵያን አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ እንደሆነም አስታውሰዋል።
በመሆኑም ሁሉም ጥቁር ሕዝቦች “ለጥቁሮች ክብርና ልዕልና ሲሉ በፓን አፍሪካ መንፈስ” ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
“ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር የወጡበት ጉዳይ ቢጠና የማጭበርበር ውጤት አካል እንደሚሆን ጥርጣሬ የለኝም”- ጠ/ሚ ዐቢይ
በመጨረሻም ትግሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ በማስታወስና ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ እንደሆነ በመግለጽ “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ። ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ፡፡ የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ ዐቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ፡፡ በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ ዐቅማቸው ይከውናሉ”ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመግለጫቸው።
ጊዜው ከዚህ በኋላ “በሩቁ ተቀምጠን ተቺና አራሚ የምንሆንበት አይደለም” ም ብለዋል፤ ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ ማንም ሊመጣ እንደማይችል በማስታወቅ።