ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ የነበሩ 320 የህወሓት ቡድን አባላት መደምሰሳቸውን መከላከያ አስታወቀ
ጀነራሉ የቡዱኑ ርዝራዦችን ለማደን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል
ከተደመሰሱት ውስጥ ቀደም ብለው የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩ እና የሸሹ ይገኙባቸዋልም ነው የተባለው
ከሱዳን በሐምዳይት በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ 320 የህወሓት ቡድን አባላት መደምሰሳቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከ320ው ውስጥ የተማረኩ የቡድኑ አባላት መኖራቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው ከመከላከያ ሰራዊት የተሰረቁ እና የወጡ ሳተላይት ስልኮች፣የሬድዮ መገናኛዎች እንዲሁም መድሃኒቶች በሰራዊቱ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።
ቡድኑ ከሱዳን መከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጋር ሲያደርገው የነበረውን ሚስጥራዊ ግንኙነት የሚያመለክቱ መረጃዎች ተገኝተዋልም ብለዋል፡፡
የቡድኑ አባላት ከውጭ በሶስት ቡድን ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ እና ረጅም ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር እንዳሉት እንደ ብ/ጄ ተስፋዬ ገለጻ አንደኛው ቡድን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ እና አባላቱ ቀደም ብለው የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩና የሸሹ ነገር ግን ቡድኑን ሲደግፉ የነበሩ ናቸው፡፡
ሁለተኛው ቡድን ሱዳን ካርቱም ሆኖ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን ሶስተኛው በሀገር ውስጥ የነበረ ነው፡፡
በሀገር ውስጥ የቀሩ የቡድኑን አባላት ለማደን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ብርጋዴር ጄነራሉ “መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እያደረስን ነው” በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህወሓት በቅርቡ በአሸባሪነት መፈረጁ የሚታወስ ነው፡፡