የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኦነግን አዲስ አመራሮች እንደማይቀበል አስታወቀ
ኦነግ በምርጫው ለመሳተፍ እና እጩዎች ለማቅረብ ያቀረበውን ጥያቄ ማየት እንደማያስፈልገውም ገልጿል
ቦርዱ በአቶ አራርሶ ቢቂላ ቡድን የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም ብሏል
በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦነግ ክንፍ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ የአመራር አባላትን መምረጡን መግለጹ ይታወሳል፡፡ በዚህም አቶ አራርሶ ቢቂላን ሊቀመንበር ፣ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ ብርሃኑ ለማ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው ነበር፡፡
ፓርቲው በውስጥ ችግሩ ምክንያት የጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሂድ በመቆየቱ “የምርጫና የእጩ ምዝገባ ጊዜ አልፎብናል” በማለት ቦርዱ የነበረበትን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለት ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲያጸድቅለት ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁም ይታወሳል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የቀረቡትን ሰነዶች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት መርምሮ ባሳለፈው ውሳኔ አዲስ የተመረጡትን አመራሮች እና የተካሔደውን ጉባኤ አልቀበልም ብሏል፡፡
የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም ሲል ቦርዱ ዛሬ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ. ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ውሳኔውን መሰረት በማድረግም በዚህ ጉባኤ የተመረጡትን አዲስ አመራሮች እንደ ኦነግ አመራሮች መቀበል እንደማይችልም ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በምርጫው ለመሳተፍ እና እጩዎች ለማቅረብ ያቀረቡትን ጥያቄ አሁን የተመረጠው አመራር ተቀባይነት ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ ቦርዱ ጥያቄውን ማየት እንደማያስፈልገው ነው ያስታወቀው፡፡
የፓርቲው ጥያቄ
ፓርቲው ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፡ ያደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙትን አባላት ስም ዝርዝርና ፊርማ፣ በመጋቢት 5 ቀን 2013 ዓም ያደረገውን የድርጅቱን ብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባኤ፣ የተሻሻለውን የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ በኦሮሚኛ የተመዘገበና በአማርኛ የተተረጎመ ሰነድ፣ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን፣ ምላተጉባኤው የተሟላ መሆኑን በማሳየት ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተደረጉት ማስተካከያዎች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የተደረገ መሆኑን ገልጾ ጠቅላላ ጉባኤው እውቅና እንዲያገኝለት ጥያቄ አቅርቧል።
ቦርዱ የፓርቲውን ጥያቄ ላለመቀበሉ ያስቀመጣቸው ምክንያቶች፡
1. ፓርቲው መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም የተደረገውን የጠቅላላ ጉባኤ ማስፈጸም የሚችለውን አስፈጻሚ ኮሚቴን ያቋቋመበት ስብሰባ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 23(4) በተመለከተው መሰረት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው 2/3ኛ አባላት በተገኙበት መሆን ሲገባው የተባለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ 2/3ተኛ አባላት የተገኙበት ሳይሆን በሦስት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ ያከናወኑት ምልዓተ ጉባኤው ያልተሟላ ስብሰባ ነው። ስለዚህ የጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የተቋቋመው ኮሚቴ በደንቡ መሰረት ምልዓተ ጉባኤ ሳይሟላ የተቋቋመ በመሆኑ የጠቅላላ ጉባኤውን መጥራትና ማስፈጸም አይችልም ሲል ወስኗል።
2. በሌላም በኩል በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 16.2 የጠቅላላው ጉባኤ የሚያቅፋቸውን አካላት በግልጽ የተመለከቱ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ሊሳተፋ የሚገባቸው የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት፣ሙሉ የአባልነት መብት ያላቸው የቀድሞ የኦነግ አመራር አባላት፣ በየደረጃው ከሚገኝ መዋቅር የሚወከሉ የኦነግ አባላት፣ ለኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል የተለየ ድርሻ በማበርከት የሚታወቁ ሰዎች (የጉባኤተኛው 5% የማይበልጡ)፣ ከፓርቲው ጋር በቅርበት በመስራት ላይ የሚገኙ ህዝባዊ ድርጀቶች ማለትም የሴቶች ፣ወጣቶች፣ ባለሙያዎች …ወዘተ ማህበራት ተወካዩች (ብዛታቸው በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚወሰን) መሆናቸው ተመልክቶ እያለ ፓርቲው አካሄድኩት በማለት ባቀረበው የጠቅላላ ጉባኤ የተካፋዩች ዝርዝር ከፍ ብሎ የተመለከቱት ጉባኤው የሚያቅፋቸው አካላት መኖራቸው አልተመለከተም፣ በመሆኑም ተሳታፊዎቹ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለመወከላቸው ቦርዱ ማረጋገጥ አልቻለም።
3. እንዲሁም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 17.1 ተወካይ ሆኖ ለጠቅላላ ጉባኤ የሚመረጥ አባል ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ ያገለገለና ግዳጁን በአግባቡ የፈጸመ መሆን እንዳለበት በሚደነግገው መሰረት መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የተሳተፉ አባላት ይህንን በደንቡን የተመለከተውን መስፈርት ማሟላታቸው ለማረጋገጥ የቀረበ ነገር የለም።
4. የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባኤ የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ጠቅላላ ጉባኤ ለማከናወን ከአመራሮቹ ውዝግብ በፊት ተቋቁሟል የተባለ ኮሚቴ እውቅና ውጪ የሆነ የድርጅቱን ህገደንብ እና አሰራር የተከተለ አይደለም በማለት ለቦርዱ ተቃውሞ የቀረበበት መሆኑንም ተገንዝቧል።
5. ቦርዱ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ የፓርቲው አመራሮችን ፣ መዋቅሮቹን እና አባላቶቹ የተለያዩ በፓርቲው ህገ ደንብ ላይ በተቀመጡ መንገዶች በመጠቀም በጠቅላላ ጉባኤ ችግሩን እንዲፈቱ የወሰነ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ይህንን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ጉባኤ መሆኑን አያሳይም። ጠቅላላ ጉባኤውን የሚያደራጅ ኮሚቴ ያቋቋሙትም ሶሰት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ መሆናቸው፣ ቦርዱ ጥር 19 ቀን ከወሰነው የፓርቲው አመራሮች መዋቅር እና አባላቶች የተለያዩ ህጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አለባቸው ከሚለው አንጻር ሲታይ የቦርዱን ውሳኔ አያሟላም።