ኦነግ ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ አዲስ አመራር መምረጡን የፓርቲው አንደኛው ቡድን አስታወቀ
በአቶ አራርሶ ቢቂላ ቡድን የተደረገው ጉባዔ “ሕገ ወጥ ነው” በቲ ኡርጌሳ
“ጉባዔ ያደረግነው የምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት ነው“ አቶ ቀጄላ መርዳሳ
ለወራት በክፍፍል የቆየው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጠቅላላ ጉባዔ ማድረጉን እና አዲስ አመራር መምረጡን የፓርቲው አንደኛው ቡድን አስታውቋል፡፡
በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ ለሁለት ቀናት ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ አራርሶ ቢቂላን ሊቀመንበር ማድረጉን አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉባዔም የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ ብርሃኑ ለማ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል ተብሏል፡፡ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት እና በጠቅላላ ጉባዔው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ ቀጄላ መርዳሳ “ኦነግ ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት ነው” ብዋል፡፡ በዚህ ጉባዔ ከ 500 በላይ አባላት መገኘታቸውን እና ይህም ሰነድ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላኩን አስታውቀዋል፡፡ በጉባዔው 43 ድምጽ የሚሰጡ (ቋሚ) እና 5 ተለዋጭ (ድምጽ የማይሰጡ ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መመረጣቸውን አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ቡድን ግን፣ በእነ አራርሶ ቢቂላ ተደርጓል የተባለው ጠቅላላ ጉባዔ “ሕገ ወጥ እንደሆነ” ገልጿል፡፡ የቡድኑ ጊዜያዊ ቃል አቃባይ አቶ በቲ ዑርጌሳ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የግንባሩን የጠቅላላ ጉባዔ አጠራር ሂደት ያልተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለጉባዔ ተብሎ የተዋቀረ የጠቅላላ ጉባዔ ኮሚቴ መኖሩን ያነሱት አቶ በቲ ፣ ኮሚቴውተደርጓል ስለተባለው ጉባዔ መረጃ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በሕገ ደንቡ መሰረት ለጉባዔ የሚጠራ ሰው የሚወከለው ከየወረዳው እንጂ በዘፈቀደ አይደለም ብለዋል፡፡ በእነ አቶ አራርሶ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሰዎች “ከሱሉልታ ብቻ በአውቶቡስ የመጡ ናቸው” ብለዋል፡፡
በጉባዔ መሳተፍ የሚችሉት ሰዎች ለሶስት ዓመትና ከዚያ በላይ የግንባሩ አባል መሆን እንደነበረባቸው ያነሱት አቶ በቲ ፣ አሁን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡት መካከል አቶ ብርሃኑ ለማ የኦነግ አባል እንዳልሆኑ ነው ያነሱት፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ መደረግ የነበረበት በማዕከላዊ ኮሚቴው ሲሆን ይህንንም የሚያደርጉት ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ መሆን እንደነበረባቸው አንስተው፣ የተደረገውን ጉባዔ ግን አቶ ዳውድ እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡ አቶ በቲ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉባዔ እንዲደረግ የወሰነው ሁለቱም ቡድኖች ባሉበት እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡ የእነ አቶ አራርሶ ቡድን በበኩሉ አቶ ዳውድ ጉባዔ እንዲደረግ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ሁለት ታዛቢዎቹ ተገኝተዋል ቢባልም ፣ ተደርጓል የተባለውን ጉባዔ በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተባለ ነገር የለም፡፡ ቦርዱ ከዚህ ቀደም በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ እልባት የሚያገኘው በድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ብቻ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡
ምርጫ እና ኦነግ
አቶ ቀጄላ መርዳሳ ምንም እንኳን የዕጩዎች ምዝገባ ቀነ ገደብ ቢጠናቀቅም “ምርጫ ቦርድ ኦነግ ያለበትን ሁኔታ አይቶ የሚያራዝምላቸው ከሆነ በምርጫው ሊሳተፉ እንደሚችሉ” ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
አቶ በቲ ኡርጌሳ በበኩላቸው የምርጫውን ጉዳይ በተመለከተ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና መንግስትን ጠይቀው ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡ የእነ አቶ ዳውድ ቡድን አሁን ላይ ምርጫ መደረግ አለበት ብሎ እንደማያምንም አቶ በቲ አስታውቀዋል፡፡ “ሀገር ችግር ላይ ናት” ብለው እንደሚምኑ የገለጹት አቶ በቲ፣ ሀገራዊ ሁኔታው ለዚህ ምቹ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡