“በምርጫ የመሳተፍ ዕድላችን 50 በመቶ ነው” አቶ ቀጄላ መርዳሳ የኦነግ የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ
“የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲደረግ ፍላጎት እንደሌላቸውም” ተናግረዋል
የፓርቲው የውስጥ ክፍፍል ኦነግ ለምርጫ እንዳይዘጋጅ ማድረጉን አቶ ቀጄላ ገልጸዋል
ምርጫ 2013 ሊካሔድ እየተቃረበ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በምርጫው ለመሳተፍ እውቅና ከተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በራሱ የቤት ስራ ተጠምዷል፡፡
አሁን ላይ ካለው የአመራር መከፋፈልና አለመግባባት ጋር በተያያዘ ኦነግ በምርጫው ይሳተፋል ወይስ አይሳተፍም የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግንባሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀጄላ መርዳሳ “በምርጫው የመሳተፍ ዕድላችን 50 በመቶ ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም 50 በመቶ ያለመሳተፍ ዕድል እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ቀጄላ ፣ ግንባሩ ሙሉ ለሙሉ ለምርጫው እንዳይዘጋጅ ያደረገው የውስጥ ክፍፍሉ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ላለፉት ሰባትና ከዛ በላይ ወራት በውስጥ ችግር ተጠምደው እንደቆዩ ያነሱት ኃላፊው አሁን ባለው ሁኔታ “ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ብቻቸውን እየወሰኑ እንደሆነ” ገልጸዋል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ቀጄላ ምርጫ ቦርድ ከአቶ ዳውድ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት እንዲያቆም ጠይቀናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አባላት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተለያዩ ማጣራቶችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ያለውን አለመግባባት በስራ አስፈጻሚ አመራሮቹ ሊፈታ ባለመቻሉ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አባላት ይህንን አውቀው ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያከናውኑም ቦርዱ ወስኗል፡፡ ይሁንና በክፍፍል ውስጥ የሚገኘው ኦነግ እስካሁን ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አልቻለም፡፡
አቶ ቀጄላ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት ፣ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይደረግ ያደረጉት የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳና ከእርሳቸው ጋር የተሰለፉ የአመራር አካላት መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ አቶ ቀጄላ እንደገለጹት ቦርዱ ስለጉባዔው ለማወያየት የግንባሩን ሊቀመንበር ጨምሮ ስራ አስፈጻሚ አባላትን ቢሮው ድረስ ጠርቶ የነበረ ሲሆን አቶ ዳውድ ግን አልተገኙም፡፡ “ጸብ ውስጥ የገባ ሰው በሶስተኛ ወገን ቢነጋገር ነበር ጥሩ” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ፣ አቶ ዳውድ ግን በጉዳዩ ላይ ከመነጋገር ይልቅ መራቅ እንደጀመሩና አመራሩን ለመበተን እንደፈለጉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ አሁን ያለውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመበተንና የራሳቸውን መዋቅር የመዘርጋት ፍላጎት እንዳላቸው ያነሱት አቶ ቀጄላ የዚህ ምክንያትም አሁን ያለው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “አቶ ዳውድ እንደፈለጉ የሚጠመዝዙት ስላልሆነ ነው” ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡ “አቶ ዳውድ መፍትሄ የሚባሉትን ሁሉ ዘግተዋል” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የመጨረሻው መፍትሄ ግን ጉባዔውን ማድረግ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ሰዎች እንደታሰሩ እና ቢሮው እንደተዘጋ ገልጸው አሁን ላይ ጉባዔ ማድረግ እንደማይቻል መናገራቸውን ያነሱት አቶ ቀጄላ ይህ በሊቀመንበሩ የቀረበው ምክንያት “ሰንካላ ምክንያት ነው” ብለዋል፡፡ ሰው ታስሯል የሚለው ምክንያት ሊሆን እንደማይችል የሚሉት አቶ ቀጄላ ኦነግ በትጥቅ ትግል ላይ እያለ ፣ጦርነትም እየተካሄደና ሰውም እየሞተ የማዕከላዊ ኮሚቴ ፣ የሥራ አስፈጻሚና የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባዎች ሁሉ ሲካሄዱ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
የግንባሩ አባላት በሚሊዮን የሚቆጠሩ በመሆናቸው ከነዚህ መሃል ለጠቅላላ ጉባዔ የሚቀርበው ከ 500 ሰው በላይ በመሆኑ የእኛ አቋም ጉባዔውን ማድረግ ነውም ብለዋል አቶ ቀጄላ፡፡ ሊቀመንበሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም አመራር መስጠት እንዳልቻሉ በማንሳት ፣ ጠቅላላ ጉባዔው ካልተደረገ የድርጅቱ ቁመና እየተበላሸ እደሚሄድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ችግር ላይ ንግግር ተደርጎ አዲስ አመራር ማምጣት እንደሚገባ ያስታወቁት አቶ ቀጄላ ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው የግንባሩ ቡድን የቦርዱን ውሳኔ መቀበሉንና ሊቀመንበሩ ተሳተፉም አልተሳተፉም ጉባዔ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልጸዋል፡፡ ጉባዔ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን በመጠቆም “አቶ ዳውድ ጉባዔ ቢደረግ ከአመራርነት እነሳለሁ የሚል ስጋት አለቸው” ሲሉም ሊቀመንበሩ ጉባዔ እንዲደረግ ያልፈለጉበትን ተጨማሪ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም ምርጫ ቦርድ “እኛ ያለንበትን ሁኔታ ተገንዝቦ አንዳንድ ጉዳዮችን ፣ በተለይም የጊዜ ሰሌዳዎችን በተለየ ሁኔታ እንዲያራዝምልን ጠይቀናል ፤ ለወደፊትም እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የኦነግን አለመግባባት እና ሌሎች ችግሮች በተመለከተ በአቶ ዳውድ በኩል ያለውን አስተያየት ለመጠየቅ ጥረት አድርጓል፡፡ ይሁንና የአቶ ዳውድ የእጅ ስልክ ሊሰራ ባለመቻሉ ሃሳባቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም፡፡