“ሕገ መንግስት እንዳይሻሻል የሚፈልግ ያለ አይመስለኝም” ቀጄላ መርዳሳ የኦነግ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
“የኦነግ ሸኔ ሰራዊት ውስጥ እኛ ያስተማርናቸው እና ያደራጀናቸው ብዙ የሉበትም“ ብለዋል
“እስከ መገንጠል“ የሚለው የሕገ መንግስቱ ሀረግ አሉታዊ ትርጉም እንዳለው አቶ ቀጄላ ገልጸዋል
በ1987 ዓ.ም በሥራ ላይ የዋለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በመንግስት መሪዎችና በተቃዋ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲተች ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ሕገ መንግስቱ የጠራና የነጻ ነው መነካት የለበትም ሲሉ በሌላ ጎራ ያሉት ደግሞ መሻሻል እንዳለበት ያነሳሉ፡፡
ኦነግ እና ሕገ መንግስት
በሽግግሩ ወቅት የቻርተሩ ተወያይ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ነው፡፡ ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግንባሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀጄላ መርዳሳ ሕገ መንግስት በየጊዜው መሻሻል ያለበት ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ሕገ መንግስት እንዳይሻሻል የሚፈልግ ያለ አይመስለኝም“ የሚሉት ኃላፊው ጉዳዩ የትኛው አንቀጽ ይሻሻል ፣ የትኛው አይሻሻል የሚለው እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ሕገ መንግስቱ ሲዘጋጅና ሲጸድቅ ተገቢ ውይይት እንዳልተደረገበት በተቺዎቹ የሚነሳ ሲሆን ሁሉም የሕዝብ ተወካዮች ደግሞ አለመወከላቸቸው ሌላው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡
አቶ ቀጄላ ሕገ መንግስት የትም ሀገር እንደሚሻሻለው ሁሉ በኢትዮጵያም ሊሻሻል እንደሚችል ያነሱ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት ብለው እንደማያምኑ ግን ተናግረዋል፡፡ “የሕገ መንግስቱ መሰረቱ እንዲቀየር አንፈልግም ፤ ምሰሶው አይቀየርም ፤ ከስር መሰረቱ ከተቀየረ ሀገሪቷን ለአደጋ ያጋልጣል ፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን ቀዶ ሌለ ማምጣት ሀገሪቷን በትኖ እንደገና መሰብሰብ ነው“ ብለዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ሕገ መንግስት የሚሻሻሉ አንዳንድ አንቀጾች እንዳሉት ነው አቶ ቀጄላ ያነሱት፡፡
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው” ይላል፡፡ በዚህ ውስጥ “እስከመገንጠል“ የሚለው ሀረግ ብሔራዊ አንድነትን አያጠናክርም ፤ አብሮነትና አንድነትን አይሰብክም በሚል ለረጅም ጊዜ የክርክር አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ “እስከ መገንጠል“ የሚለውን ቃል በሌላ መንገድ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ “መገንጠል“ የሚለው አሉታዊ ትርጉም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ “እያንዳንዷ አንቀጽ ታይታ መስተካከል የሚገባው ይስተካከላል ፤ “እስከ መገንጠል“ የሚለው ተነሳ አልተነሳ ህዝቡ የራሱን እድል በራሱ መወሰን ይችላል ከተባለ ህዝቡ ያንን ወደፈለገው ሊተረጉመው ይችላል“ ብለዋል አቶ ቀጄላ፡፡
ኦነግ እና ኦነግ ሸኔ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ በትጥቅ ትግል ላይ ባለው የኦነግ ሸኔ ቡድን ውስጥ ያሉት አባሎች በርካታው አዳዲሶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ “አሁን እዛ ያለው ሰራዊት ውስጥ እኛ ያስተማርናቸው እና ያደራጀናቸው ብዙ የሉበትም ፤ አዳዲስ ናቸው“ ያሉት አቶ ቀጄላ እብዛኛው አባላት በቅርብ ጊዜ እንደተቀላቀሉ አስታውቀዋል፡፡ የሸኔ አባላት “ምን አይነት ስልጠና እንዳላቸው ፣ ምን አይነት የፖለቲካ ትምህርት እንደሚማሩ“ እንደማያውቁ ያነሱት አቶ ቀጄላ ቀደም ሲል የነበሩትን ግን እራሱ ኦነግ ያሰለጠናቸው እና የፖለቲካ ትምህርት ያስተማራቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ “የትጥቅ ትግል“ እያደረጉ ባሉት ውስጥ ኦነግ ያሰለጠናቸው የቀድሞዎቹ አባሎች የሉም ማለት እንዳልሆነ ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል፡፡
የአቶ ዳውድ ኢብሳም ሆነ የአቶ አራርሶ ቢቂላ ቡድን ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አለው ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ቀጀላ ኦነግ እና ኦነግ ሸኔ ግንኙነት እንዳላቸው ማስረጃ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡