ጥምቀት የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ተመዘገበ።
በኮሎምቢያ ቦጎታ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ያለው የዓለም አቀፉ የባህል የሳይንስና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግስታት ኮሚቴ ጥምቀት አንዱ የማይዳሰስ አለማቀፋዊ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ትናንት ረቡዕ ታህሳስ 01 ቀን 2012ዐ.ም. ከሰዓት በኋላ ወስኗል።
ጥምቀት በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ደማቅ ኃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ነው ያለው ኮሚቴው የክርስቶስን በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ ታሳቢ እንደሚያደርግ አስታውሷል።
ለውሳኔው ምስጋና ያቀረበውና የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን ያስተላለፈው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሃገራትን በማግባባት ረገድ ለነበራት ሚና እና ላሳየችው ወንድማዊ ትብብር ጅቡቲን አመስግኗል። ጅቡቲ የኮሚቴው አባልም ናት።
ኤምባሲው ውሳኔውን ደግፈዋል በሚልም ሴኔጋልን፣ ካሜሩንን፣ ቶጎን፣ ሞውሪሺዬስን፣ ዛምቢያን፣ ኩዌትን፣ ፍልስጤምን፣ አዘርባጃንን፣አርመንን፣ ቻይናን፣ ፖላንድን፣ ሊባኖስን፣ ጃማይካን፣ ቆጵሮስን፣ ካዛኪስታንን እና ኩባን አመስግኗል።
ጥምቀት ከመስቀል በዓል፣ከገዳ ስርዓት እና ከፍቼ ጨምበላላ በመቀጠል በ4ኛነት በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የኢትዮጵያ ሃብት ነው።
ጥምቀትን ጨምሮ የዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ የፈረንሳይ ጣልያን እና ስዊዘርላንድ (በጋራ)፣ የኢራን፣ የሜክሲኮ እና ስፔን (በጋራ) ሃብት ናቸው የተባሉ ቅርሶችን የመዘገበው ኮሚቴው እስከ ጉባኤው ማጠናቀቂያ ሌሎች ቅርሶችን እንደሚመዘግብም በድረገጹ አስታውቋል።