ማርን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለዉ ሲያሰራጩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
በአማራ ከልል ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ማርን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ሲያሰራጩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ እንደገለጹት ግለሰቦች የተያዙት ትላንት ከሰዓት በኋላ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባደረገው ክትትል ነው። በከተማው 03 ቀበሌ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ባዕድ ነገሩን በማዘጋጀት ላይ የነበሩ ሦስት ሴቶችን ጨምሮ ሁለት ወንድ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ባዕድ ነገሩን በዋናነት የሚያቀነባብሩ ቀሪ ከሦስት በላይ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝም ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ማሩንስኳር፣ ማር መሳይ ፈሳሽ ነገርና ከውጭ አገር የሚመጣ ማር የሚያስመስል ኬምካል በመጠቀም ያዘጋጁት እንደነበረ መረጋገጡንም አስረድተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ባዕድ ነገሩን ስኳር፣ ማር መሳይ ፈሳሽ ነገርና ከውጭ አገር የሚመጣ ማር የሚያስመስል ኬምካል በመጠቀም በበርሜል እሳት ላይ ጥደው ከተዋህደ በኋላ አውጥተው በማቀዝቀዝ ማር ሲመስል በኩንታል ጭነው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ይሸጡ እንደነበርም ተረጋግጧል።በእለቱ አፍልተው ያረጉትና ወደ ሌላ ቦታ ሊጫን የነበረ ከሰባት ኩንታል በላይ ከባዕድ ነገር የተሰራ ማር መሰል ውህድ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጠቁመዋል።“ግለሰቦቹ ከፍተኛ ቅንጅታዊ አሰራርና ጥንቃቄ ከማድረጋቸውም ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ መሳሪያ እያሳዩ እንገድላችኋለን በማለት ያስፈራሩ እንደነበረም ለማወቅ ችለናል” ብለዋል የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ።
በቁጥጥር ስራ የዋሉት አምስት ግለሰቦችም ጉዳያቸው በህግ እየታየ ሲሆን የተያዘው ባዕድ ነገር በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በባለሙያ እንደሚጣራም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ ኢዜአ