ብልጽግና ስብሰባዎቹ ኮሮናን በተመለከተ ግንዛቤን ማስጨበጫ መድረኮች ናቸው ብሏል
ብልጽግና ስብሰባዎቹ ኮሮናን በተመለከተ ግንዛቤን ማስጨበጫ መድረኮች ናቸው ብሏል
የዓለም ስጋት የሆነውና በርካቶችን እያጠቃ ያለው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተገኘ በኋላ መንግስት እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ በቅድሚያም ነጋዴዎች የዋጋ ንረት እንዳያስከትሉ፣ ህዝቡ ንጽህናውን እንዲጠብቅና ርቀቱን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስም መመሪያዎች እየተላለፉ ነው፡፡
ቫይረሱ በአንድ ጃፓናዊ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከተገኘበት መጋቢት 4 ቀን ጀምሮም በበርካታ ነጋዴዎች ላይ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መመሪያ መሰረትም ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ስፖርታዊ ውድድሮችም ተቋርጠዋል፡፡ ይሁንና እርሳቸው በፕሬዝዳንትነት የሚመሩትን ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ግን በተለያዩ አካባቢዎች ስብሰባዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡
በዚህም መሰረት በአማራ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች፣ በደቡብ ወሎ ዞን፣በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፣ ብልጽግና ፓርቲ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡
ቅርንጫፍ ለመክፈት በሚል የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ በከሚሴ ከተማ ያደረገው ስብሰባም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ በኋላ የተካሄደ ነው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከል ርቀትን መጠበቅ እንደሚበጅ ቢመክሩም ስብሰባዎቹ ግን አሁንም አልቆሙም፤መካሄዳቸውም ቀጥሏል፡፡
በክልሉ በመካሄድ ላይ ስላሉት ስብሰባዎች የጠየቅናቸው አንድ የአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ከፍተኛ አመራር እየተካሄደ ያለው ስብሰባ ሳይሆን ለአመራሮች መመሪያ የማስተላለፊያ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ “ስብሰባ ነው እየተካሄደ ያለው የሚለው ውሸት ነው” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የፓርቲው የውጭና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወሉ አብዲም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
“እየተካሄደ ያለው ስብሰባ አይደለም፣ይልቁንም እየተስፋፋ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መሰረት በማድረግ አመራሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ለማድረግ እንደሚያስችል የታመነበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ነው” ሲሉም ነው የሚያስቀምጡት፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል የአመራሩ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለማስገንዘብ በማሰብ የሚካሄድ ነው የተባለለት ይህ መድረክ ለወረርሽኙ አያጋልጥም ወይ በሚል የተጠየቁት ኃላፊው “የጤና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ እንዲሰጡ እየተደረገ ነው” በሚል መልሰዋል፡፡
“በአንድ ክፍል ውስጥ ከ10-20 ሰዎች ብቻ እንዲገኙ በማድረግ ርቀትን ጠብቆ (ሶሻል ዲስታንስ)” በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአካባቢንና የግል ንጽህናን የመጠበቅ ዘመቻዎችም አሉ ብለዋል አቶ አወሉ፡፡
እነዚህ ስብሰባዎች እስከ መቼ ይቆያሉ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ገና ያልተጀመረባቸው ቦታዎች መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን እንደክልሎች ነባራዊ ሁኔታ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ስ ብሰባውን ገና አልጀመረም በሚልም አዲስ አበባን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
የፓርቲው የስራ ሃላፊዎች ይህንን ይበሉ እንጅ በተለያዩ አካባቢዎች የተደረጉት ስብሰባዎች ርቀትን ያልጠበቁና በጣም መጠጋጋት ያለባቸው ናቸው በሚል በማህበራዊ የትስስር ገጾች ጭምር በመተቸት ላይ ይገኛሉ፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ይበልጥ ሊያባብሰው እንደሚችልም ነው የሚጠቀሰው፡፡
ከዛሬ ጀምሮም በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የብልጽግና ፓርቲ አባላት ስብሰባ ሊያደርጉ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡