ሱዳን ደቡብ ሱዳን ያቀረበችውን የአደራዳሪነት ጥያቄ እንደሚቀበሉት አስታወቁ
ኢትዮጵያ ሱዳን ወደነበረችበት እንድትመለስና ጉዳዩ በድርድር እንዲፈታ ገልጻለች
የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን መከላከያ ወደ ትግራይ ክልል በመሰማራቱ የተፈጠረውን ክፍተት ተከትሎ የኢትዮጵያን ድንበር መጣሷን እየገለጸች ነው
ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የድንበር ግጭት በሰላም እንዲፈቱ ለማደራደር ያቀረበችውን ጥያቄ ሀገራቸው እንደምትቀበል የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አስታወቁ፡፡
ጁባ ያቀረበችውን ሃሳብ በበጎ እንደሚቀበሉት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ“የአፍሪካን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት” የተወሰደ ጥረት ነውም ብለውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የደቡብ ሱዳን የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴንግ አሎር ኩኦልን በካርቱም ማነጋገራቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የተላከ የአደራዳሪነት ጥያቄን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አስረክበዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ሀገራቱ ያላቸውን የድንበር ላይ ውዝግብ በሰላም እንዲፈቱ ቀደም ሲል መጠየቋ የሚታወስ ነው፡፡ ጁባ በኋላ ላይ አዲስ አበባና ካርቱም የድንበር ላይ ውዝግባቸውን በሰላም እንዲፈቱ ያደራዳሪ ሚና እንደምትወጣ ገልጻለች፡፡ ሀገሪቱ አደራዳሪ መሆን እችላለሁ ያለችውን ሀሳብ ሱዳን በበጎ እንደምትቀበለው ነው ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የገለጹት፡፡
አብደላ ሃምዶክም ጁባ ሀገራቱን ለማነጋገር ላቀረበችው ሃሳብ ምስጋናቸውን አቅርበው ይህ ድርጊት የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማረጋገጥ የተወሰደ ቁርጠኝነት እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡ ከደቡብ ሱዳን የቀረበውን ሀሳብ ሀገራቸው እንደምትቀበል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ይህ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ ለመፍታት የተወሰደ ቁርጠኝነት ነው ብለዋል፡፡
የሱዳን ባለሥልጣናት ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ላይ ውዝግብ ለሌሎች ሀገራት ለማሳወቅ ወደ ካይሮ፣አስመራ፣ጁባና ሳዑዲ አረቢያ መላካቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሱዳን ጋር የገባችበት የድንበር ላይ ውዝግብ በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንደሚፈታ እንደምትፈልግ መግለጿ ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ዲና ሱዳን ድንበር ጥሳ መግባቷንና ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ኢትጵዮጵያ እንደምትፈልግና ለጦርነት እንደማትቸኩልም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር መጣሷንና ይህን ያደረገችው ጦሩ በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ዘመቻ መሰማራቱን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት በማየት መሆኑን ገልጿል፡፡