የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ 50 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ተባለ
የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 99.2 በመቶ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች 79 በመቶ ደርሷል
የህዳሴ ግድብ ግንባታ በቀጣዩ ዓመት በ2017 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ 50 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ አስታውቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ይህንን ያስታወቁት።
ኢንጅነር ክፍሌ የግድቡ ግንባታ አሁን ስለደረሰበት ደረጃ ሲያብራሩም፤ የህዳሴ ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ 99 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በዚህም ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት ውስጥ የ10 ነጥብ 65 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 99 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 79 በመቶ መድረሱንም ነው ሥራ አስኪያጁ ያስታወቁት።
እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለፃ የውሃ ማስተላለፊያና መቆጣጠሪያ የብረታብረት ሥራዎች አጠቃላይ አፈፃፀም 90 በመቶ ተከናውኗል።
እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም ድረስ ለፕሮጀክቱ ግንባታ 191 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉነ ያስታወቁት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ቀሪ የግድቡን የግንባታ ሥራዎች ለማጠናቀቅም 50 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪካ ኃይል መረጃ ያመለክታል።
የኮንትራት ማሻሻያ መደረጉ፣ የተጣበበ የፕሮጀክት ጊዜ ሰሌዳና በግንባታ ወቅት በግድቡ መሠረት ላይ ያጋጠመ ልል ድንጋይ መኖሩ እንዲሁም የልምድ ማነስ እና የጥራትና ልኬት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ ከዚሀ ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ግድቡ በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ2017 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ ተገንብቶ ኢትዮጵያውያንና ጎረቤቶቿን ማገልገል እንደሚጀምር መግለጻው ይታወሳል።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ፕሮጀክቱ በቀጣይ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል። ይህም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነበር በይፋ የተጀመረው።
ከ13 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።
የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ግድቡ ካሉት ተርባይኖች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ዩኒት 10 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
በነሃሴ ወር 2014 ላይ ደግሞ ዩኒት 9 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 540 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨም ይገኛል።